የዓለም ጤና ድርጅት ደቡብ አፍሪካ በአስትራዜኔካ ክትባት ላይ ያስተላለፈችው ውሳኔ አሳስቦኛል አለ

ክትባት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የዓለም ጤና ድርጅት ከኮሮናቫይረስ ክትባቶች ጋር በተያያዘ በችኮላ ከውሳኔ ላይ መድረስ እንደማያስፈልግና ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ ስራዎች መከናወን እንዳለባቸው አሳሰበ።

ድርጅቱ ይህን ያለው አንድ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የተሰራ ጥናት የአስትራ ዜኔካ ክትባት በደቡብ አፍሪካ የተመዘገበውን አዲሱን የቫይረስ አይነት መከላከል ላይ ደካማ ነው የሚል ውጤት ይዞ መውጣቱን ተከትሎ ነው።

ነገር ግን ባለሙያዎቹ ክትባቱ በቫይረሱ ምክንያት ጤናቸው በእጅጉ ለተቃወሰባቸው ሰዎች ወሳኝ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።

ተመራማሪዎች እንደሚሉት በአሁኑ ወቅት በደቡብ አፍሪካ 90 በመቶ የሚሆኑት ሰዎች እየተያዙ ያሉት በአዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ ነው።

2ሺህ ሰዎችን ያሳተፈው ምርምር ውጤት መካከለኛ እና ዝቅተኛ ምልክት በሚታይባቸው ሰዎች ላይ ክትባቱ በጣም አናሳ የመከላከል አቅም እንዳለው ያሳያል ተብሏል።

ደቡብ አፍሪካ 1 ሚሊዮን የአስትራዜኔካ ክትባት የተቀበለች ሲሆን በቀጣይ ሳምንት ክትባቱን ለዜጎቿ ለመስጠት በዝግጅት ላይ ነበረች።

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም እንደሚሉት ተመራማሪዎቹ ጥናታቸውን ሲሰሩ የተጠቀሙት ናሙና በጣም ውስን ከመሆኑም ባሻገር የጥናቱ ተሳታፊዎች "ወጣቶችና በጥሩ የጤንነት ሁኔታ ላይ የሚገኙ" ናቸው ብለዋል።

ክትባቱ ከፍተኛ ሕመምን የመከላከል አቅሙ ማወቅ እጅግ ጠቃሚ ነው ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ በሰጡት መግለጫ ላይ።

የክትባት አምራች ኩባንያዎች እራሱን እየቀያየረ ለሚገኘው የኮሮረናቫይረስ አይነት የሚሆን ፍቱን ክትባት ማምረት ላይ ትኩረታቸውን አድርገው እንዲሰሩም አሳስበዋል።

ባለሙያዎች እንደሚሉት አዳዲስ የቫይረስ አይነቶች ሲከሰቱ ለተከሰቱት ቫይረሶች የሚሆኑ ማሻሻያ የተደረገባቸው ክትባቶችን ለማቅረብ ሳምንታት ወይም ወራት ሊወስድ ይችላል።

እስካሁን የተደረጉ የመጀመሪያ ሙከራዎች እንደሚያሳዩት ሞደርና የተሰኘው ክትባት ደቡብ አፍሪካ ለተፈጠረው አዲስ የኮሮናቫይረስ ዝርያ ውጤታማ ሲሆን ዩናትትድ ኪንግደም ውስጥ ለተገኘው አዲስ የቫይረሱ ዝርያ ደግሞ የአስትራዜኔካ ፍቱን ነው ተብሏል።