ሱዳን፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ አዲስ ካቢኔ አዋቀሩ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ 25 ሚንስተሮች የተካተቱበት አዲስ ካቢኔ አዋቀሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዶክ ይህንን ውሳኔያቸውን በአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣብያ በቀጥታ በተላለፈ ስርጭት ላይ አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ "አዲሱ ካቢኔ የተዋቀረበት ዋና ዓላማ አገሪቱን ከውድቀት ለመታደግ ባለመ የፖለቲካ መግባበት ነው።" ብለዋል በጋዜጣዊ መግለጫቸው ወቅት።
አዲሱ መንግሥታቸው 25 ሚኒስትሮች እንደሚኖሩት ያስታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የትምህርት ሚኒስትር ማን ይሁን በሚለው ላይ ገና ስምምነት አለመደረሱን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዶክ በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት እንዳረጋገጡት አዲሱ መንግሥት እኤአ በ ታህሳስ ወር 2019 ለተካሄደው ሕዝባዊ አብዮት መርሆዎች ተገዢ የሚሆን ሲሆን ከዚህ በፊት የነበሩ አመራሮች የጀመሩትን ስኬት ይዞ የሚቀጥል ይሆናል።
ከዚህ በፊት የነበረው አመራር ትልቅ ስኬት በማለት የጠቀሱትም ሱዳንን አሸባሪነትን ከሚደግፉ አገራት ዝርዝር ውሰጥ ማስፋቅ ነው።
ከአዲሱ ተሿሚ ሚኒስትሮች መካከል ከዚህ ቀደም ፍትሕና እኩልነት እንቅስቃሴ የተሰኘ አማፂ ቡድን ይመራ የነበረው ጂብሪል ኢብራሂም ይገኝበታል።
የሟቹ ኢማም ሳዲቅ አል መሃዲ ልጅ የሆነችው መሪያም አል ሳዲቅ ደግሞ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሆና ተሾማለች።
በአዲሱ መንግሥት ውስጥ የተካተቱ ሰዎች ሹመት የተሰጣቸው ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር የሽግግር መንግሥቱ እና የሱዳን አብዮታዊ ግንባር (ኤስአርኤፍ) የተሰኘው የአማፂያን ቡድኖች ጥምረት በጁባ በደረሱት የሰላም ስምምነት መሰረት ነው ተብሏል።
አዲሱ መንግሥት አገሪቱ ምርጫ እስከምታካሄድበት 2024 ድረስ በሥልጣን ላይ ይቆያል ተብሏል።












