ግብጽ ከወርቅ የተሠራ ምላስ የተገጠመላቸው 2ሺህ ዓመታት ያስቆጠሩ አፅሞችን አገኘች

በግብፅ የተገኙት አፅሞች

የፎቶው ባለመብት, Egyptian Ministry of Antiquities

Presentational white space

የግብጽ በመሬት ውስጥ የተቀበሩ ቅርሶች ጥናት ተመራማሪዎች 2ሺ ዓመት ያስቆጠሩ አፅሞችን አገኙ፡፡

አፅሞቹ ወደ አፈርነት እንዳይቀየሩ በመድኃኒት አድርቆ የማቆየት ጥበብ የተጠበቁ ሲሆን ልዩ የሚያደርጋቸው ግን ምላሳቸው በወርቅ መተካቱ ነው፡፡

የግብጽና የዶሚኒካን ቡድን በአሌክሳንድሪያ ከተማ፣ በታፖሲሪስ ማግና ቤተ መቅደስ አካባቢ 16 በማድረቂያ የተጠበቁ አፅሞችን ከአለት በተሰሩ የመቃብር ቤቶች ውስጥ እንዳሉ ነው ያገኙት፡፡

ከፍ ባለ እርከን ላይ የሚገኙ ሰዎችን በዚህ መንገድ አንዳንድ የሰውነት ክፍላቸውን በወርቅ ተክቶ መቅበር በግሪክና ሮማዊያን ሥልጣኔ ዘመን የተለመደ ነበር፡፡

ምናልባት አፅሞቹ ምላሳቸው በወርቅ የተሰራላቸው ከሞት በኋላ ይኖራል ብለው በሚያምኑት ሕይወት የፍርድ ቀን ላይ ጣኦት ኦሲሪስን አቀላጥፈው እንዲያናግሩት ያግዛቸዋል በሚል እንደሆነ ተገምቷል፡፡

የጥንታዊ ግብጻዊን እምነት ጣኦት ኦሲሪስ ከመሬት በታች ያለውን ዓለም የሚመራ ጌታና የሙታን ፈራጅ እንደሆነ ይታመን ነበር፡፡

ወርቁ የተለበጠባቸው ምላሶች ጫፎቻቸው የአክሊል ምልክት ተደርጎባቸው ተገኝተዋል፡፡ ከዚህም ሌላ የኮብራ እባብ ምልክት ተገኝቷል፡፡

የአሌክሳንድሪያ የከርሰ ምድር ቅርሶች ጥናት ኃላፊ ካሊድ አቦ ኤል ሐምድ በዚህ ፍለጋ የመቃብር ውስጥ የአፅሞች ጭምብሎችም መገኘታቸውን ተናግረዋል፡፡

እነዚህ የፊት ጭምብሎች የ2ሺህ ዘመን ዕድሜ ያላቸው ናቸው፡፡

ሚስተር ካሊድ ጨምረው እንደገለጹት በዚሁ መቅደስ ስፍራ ከዚህ ቀደም የዝነኛዋ ንግሥት ክሊዮፓትራ 7ኛ ምሥል ያለባቸው ሳንቲሞች መገኘታቸውን አስታውሰዋል፡፡

ክሊዮፓትራ 7ኛ የግሪክ ተናጋሪው ቶሌማቲክ ሥርወ መንግሥት የመጨረሻዋ ንግሥት እንደሆነች ይታወቃል፡፡ የግዛት ዘመኗም ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ51 እስከ 30 ዓመተ ዓለም ነበር፡፡

ንግሥት ኪሊዮፓትራ መሞቷን ተከትሎ ነው ጥንታዊት ግብጽ በሮማዎች እጅ የወደቀችው፡፡