ለጠ/ሚ ዐብይ ድጋፍ ለመግለጽ በበርካታ የኦሮሚያ ከተሞች ሰልፎች ተካሄዱ

ለጠ/ሚ ዐቢይ ድጋፍ ለመግለጽ በበርካታ ከተሞች ሰልፎች እየተካሄዱ ነው

የፎቶው ባለመብት, OBN

በዛሬው ዕለት በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ከተሞች ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ የድጋፍ ሰልፎች መደረጋቸውን ተከትሎ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድጋፉ በተለያየ ደረጃ ላይ ያሉ የመንግሥት ባለስልጣናት ሃላፊነታቸውን በአግባባቡ እንዲወጡ የህዝብ አደራ መሆኑን መማሪያ ነው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በፌስቡካቸው ስለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነው የመንግሥት ዋነኛ ተግባር ህዝብን ማገልገል እንደሆነ አስታውሰዋል።

"የመንግስት ልዩ ተልዕኮ ህዝብን ማገልገል ብቻ ነው ፤ በየደረጃው ያለን የህዝብ አገልጋዮች ከእንደዚህ አይነት ድጋፍ የምንማረው እና መገንዘብ ያለብን ሀላፊነታችንን በአግባቡ እንድንወጣ የህዝብ ጥሪና አደራ እንዳለብን ሊሆን ይገባል።" ብለዋል።

በዛሬው ዕለት በክልሉ የተደረጉ የድጋፍ ሰልፎችን የክልሉ የቴሌቪዥን ጣቢያ ኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ (ኦቢኤን) ከተለያዩ በቀጥታ ስርጭቱ አስመልክቷል።

ኦቢኤን በቀጥታ ዘገባው በሻሸመኔ፣ ዶዶላ፣ አሰላ፣ ባሌ ሮቤ፣ ጅማ፣ በደሌ፣ አዳማ፣ ዱከም፣ ገላን፣ ሰበታ፣ ሰንዳፋ፣ ቡራዩ፣ ያቤሎ፣ ምዕራብ እና ምስራቅ ወለጋ በሚገኙ ከተሞች የድጋፍ ሰልፎች እየተካሄዱ ከሚገኝባቸው ስፍራዎች መካከል መሆናቸውን አስመልክቷል።

የክልሉ ኮሚኒኬሽን ቢሮ በበኩሉ ለጠቅላይ ሚንስትሩ የሚደረገው የድጋፍ ሰልፍ በመላው ኦሮሚያ እንደተካሄደ ገልጿል።

ኮሚኒኬሽን ቢሮው በፌስቡክ ገጹ ላይ እንዳስታወቀው ለጠቅላይ ሚንስትሩ የሚደረገው የድጋፍ ሰልፍ በነገው ዕለትም እንደሚቀጥል ይጠበቃል።

ለጠ/ሚ ዐቢይ ድጋፍ ለመግለጽ በበርካታ ከተሞች ሰልፎች እየተካሄዱ ነው

የፎቶው ባለመብት, OBN

ድጋፋቸውን ለጠቅላይ ሚንሰትሩ ለመስጠት አደባባይ ከወጡት መካከል “የአገራችን ሰላም እንጠብቃለን፣ በኃይል ስልጣን ለመያዝ የሚደረገውን ጥረት እንቃወማለን፣ በማህበራዊ ሚዲያ ለውጡን ለማደናቀፍ የሚደረገውን ጥረት እናወግዛለን” የሚሉ መፈክሮችን ሲያሰሙ በኦቢኤን በቀጥታ ስርጭቱ አስመልክቷል።

ከሰሞኑ በማሕበራዊ ድር አምባዎቻቸው ላይ ጠፍተው የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ብቅ ማለታቸው ይታወሳል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩን በአደባባይ አለመታየት በማስመልከት በማሕበራ ድር አምባዎች ያልተረጋገጡ ወሬዎች ሲሰራጩ እንደነበረ ይታወሳል።

ይህንን ተከትሎ የሃገሪቱ ብሔራዊ ደኅንነት መሥሪያ ቤት በማሕበራዊ ድር አምባዎች ላይ ሃሰተኛ መረጃዎች የሚያሰራጩ ሰዎችን አስጠንቅቆ እንደነበር ይታወሳል።