ዴሞክራቶች የትራምፕ ደጋፊ የሆኑትን ሴት ከኮንግረስ ለመፈንገል እያሴሩ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአሜሪካ ፖለቲካ ቁንጮ ከሆኑት ሁለት ፓርቲዎች መካከል አንዱ የሆኑት ዴሞክራቶች፤ የትራምፕ ደጋፊ የሆኑትን ሕግ አውጭ ከጨዋታ ውጭ ለማድረግ እየጣሩ ነው።
የሪፐብሊካን ፓርቲ አባል የሆኑት ወግ አጥባቂዋ ፖለቲከኛ በማሕበራዊ ድር አምባ ገፆቿ ላይ በጻፉት ጉዳይ ነው ከኃላፊነቷ ትነሳ እየተባለ ያለው።
ማርጆሪ ታይለር ግሪን የተባሉት ሪፐብሊካን በሴራ ትንተና ያምናሉ።
የመስከረም 9/11 የሽብር ጥቃት ሆን ተብሎ የተቀነባበረ ነው ብለው ከሚያምኑ አሜሪካዊያን መካከልም አንዷ ናቸው።
ጆርጂያ ግዛት ወኪል የሆኑት የኮንግረስ አባል ባለፈው ወር አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ጆ ባይደንን ለመክሰስ ደፋ ቀና ሲሉ ነበር።
ማርጆሪ ግሪን ባሳለፍነው ሰኞ በትዊተር ገጻቸው ላይ "ዴሞክራቶች ከተወከልኩበት ኮሚቴ ካባረሩኝ ቃል እገባላችኋለሁ እኛ በ2022 [በቀጣዩ የምክር ቤት ምርጫ] አብላጫ ድምፅ ስናገኝ አፀፋውን እጥፍ ድርብ አድርገን እንመልሳለን" ሲሉ ጽፈው ነበር።
"አብላጫ ድምፅ ማግኘታችን የማይቀር ነው፤ እሱን እንዳትሳሳቱ" ሲሉም ዝተዋል።
ባለፈው ኅዳር ወደ አሜሪካ ኮንግረስ የሚያስገባትን ድምፅ ያገኘችው ማርጆሪ በሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት የትምህርትና ሰው ኃይል እንዲሁም የበጀት ኮሚቴ አባል ሆነው ተመርጠዋል።
የኮሚቴው አባል እንዲሆኑ የመረጧቸው በምክር ቤቱ የሪፐብሊካኖች መሪ የሆኑት ኬቪን ማካርቲ ናቸው።
ዴሞክራቶቹ ለምን ሊያስወግዷቸው ፈለጉ?
ዴሞክራቶች የትራምፕ ደጋፊ የሆኑት ግለሰብ ከዚህ በፊት የፈፀሟቸው ድርጊቶች የኮሚቴ አባል እንዲሆኑ የሚያደርጋቸው አይደለም ሲሉ ይከራከራሉ።
በተለይ ደግሞ ከትምህርት ኮሚቴው እንዲፈነገሉ ነው ፍላጎታቸው።
ሴትዬዋን ከኮሚቴው የመፈንገል ሂደቱን እየመሩ ያሉት ዴሞክራቷ ዴቢ ሹልትዝ "ሪፐብሊካኖች እሷን መተካት ካልቻሉ እኛ እንተካላቸዋለን" ሲሉ ተደምጠዋል።
ትላንት [ሰኞ] በምክር ቤቱ አብላጫ ድምፅ ያላቸው ዴሞክራቶች መሪ የሆኑት ስቴኒ ሆዬር ለሪብሊካኖች መሪ 'ግለሰቧን ያውርዱልን' የሚል ጥሪ አቅርበዋል።
ማርጆሪ ከኮሚቴዎቹ በ72 ሰዓታት ውስጥ ካልወረዱ ግን ዴሞክራቶች ይህንን ጉዳይ በራሳቸው እንደሚወጡ ዝተዋል።
ዴሞክራቶች ግለሰቧ ከኮሚቴዎቹ ብቻ ሳይሆን በጠቅላላው ከኮንግረሱ እንዲባረሩ ይፈልፈጋሉ።
ከወግ አጥባቂነታቸው አልፈው አክራሪ ሆነዋል ብለው የሚያምኑ ሪፐብሊካኖችም ጭምር ማርጆሪ ከኮንግረስ እንዲባረሩ ጥሪ እያቀረቡ ነው።
በሴኔቱ አናሳ ድምፅ ያላቸው ሪብሊካኖች መሪ የሆኑት ሚች ማኮኔል ሴትዬዋ የምታምንባቸውን የሴራ ትንተናዎች 'ለሪብሊካን ፓርቲ ካንሰር ናቸው' ሲሉ ወርፈዋል።
በፈረንጆቹ 2019 በኮንግረሱ የአዮዋ ግዛት ተወካይ የሆኑት ሰው በአንድ ቃለ መጠይቅ ወቅት የነጭ የበላይነትን አጣጥለው አስተያየት በመስጠታቸው ከሁለት ኮሚቴዎች መወገዳቸው አይዘነጋም።
ነገር ግን ሪፐብሊካኖች አሁንም በፖርቲ አጋራቸው ላይ ይህን ዓይነት እርምጃ ይወስዳሉ ወይ የሚለው እርግጥ አይደለም።
አንድ የኮንግረስ አባልን ከኮንግረሱ ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ ሁለት ሶስተኛ ድምፅ ያሻል።
በአሜሪካ ታሪክ ከኮንግረስ አባልነታቸው የተወገዱ ሰዎች ቁጥር አምስት ብቻ ነው።
ማርጆሪ የኮንግረስ አባል ሆነው አነጋጋሪ አስተያየት የሰጡ የመጀመሪያዋ ሴት አይደሉም።
በ2019 የሚኒሶታዋ ኢልሃን ኦማር ፀረ-አይሁድ ናቸው ተብለው በተፈረጁ አስተያየታቸው ምክንያት ብዙ ትችት ደርሶባቸው ነበር።
በወቅቱ ኢልሃን ለሰጡት አስተያየት ይቅርታ ጠይቀው ነበር።
የትራምፕ ቀንደኛ ደጋፊዋ ማርጆሪ ግሪን ግን በተደጋጋሚ አነጋጋሪ አስተያየት ከመስጠት ባለፈው በይፋ የሴራ ትንተና አማኝ መሆናቸው ነው ለየት የሚያደርጋቸው።
ማርጆሪ፤ በ2016 የአሜሪካ ምርጫ የትራምፕ ተፎካካሪ የሆኑት ሂላሪ ክሊንተን ሕፅናትን ይገርዛሉ ብለው ያምናሉ።
አልፎም በፈረንጆቹ 2001 የደረሰው የ9/11 አደጋ የአሜሪካ መንግሥት ሴራ ነው ብለው ነው የሚያምኑት።
ይህም አልበቃ ብሏቸው ካሊፎርኒያ ውስጥ የተከሰተው የሰደድ እሳት ሆን ተብሎ ከሕዋ ላይ በተለቀቀ ጨረር የተነሳ ነው ይላሉ።
በአንድ ወቅት 'ጥቁሮች የዴሞክራቲክ ፓርቲ ባሪያዎች ናቸው'፤ ነጭ ወንዶች ደግሞ አሜሪካ ውስጥ በጣም በደል የሚደርስባቸው ናቸው ሲሉ አስተያየት ሰጥተው ነበር።












