ኮሮናቫይረስ፡ ሙሉ ሕዝቧን እየከተበች ያለችው እስራኤል በክትባቱ ፍቱንነት ጥርጣሬ የገባት ለምንድነው?

የእስራኤል የህክምና ባለሙያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሕዝቧን በብዙ ቁጥር እየከተበች ያለችው እስራኤል የክትባቱን ፈዋሽነት የሚጠራጠሩ ዜጎቿ አሳስበዋታል።

ተራ ዜጎች ብቻም ሳይሆኑ የጤና ባለሙያዎቿም ስለ ክትባቱ ፈዋሽነት መጠነኛ ጥርጣሬ የገባቸው ይመስላል።

እስራኤል የኮቪድ ክትባትን በብዛት በመግዛት አገሯ አከማችታለች። በርካታ ሕዝቧን ክትባቱን ለመክተብ በከፍተኛ ዝግጅት ላይ ትገኛለች።

ዝጅግት ላይ ብቻም ሳይሆን ግማሽ ሚሊዮን ሕዝቧን ክትባት እንዲደርሰው አድርጋለች። የእስራኤል ግብ ሙሉ በሙሉ ሕዝቧን መከተብና ተህዋሲውን ታሪክ ማድረግ ነው።

እንዲያው አንዳንዶች ይቺ አገር እስራኤል ሕዝቧን "የቤተሙከራ አይጥ" ልታደርገው ነው ወይ? እስከማለት ደርሰዋል።

ይህን ስታደርግ ታዲያ ብዙ የጤና አዋቂ ሳይንቲስቶች ዐይናቸውን በዚያች አገር ላይ ጥለዋል። ለምን? ዋናው ምክንያት በእስራኤል የሚታየው የክትባት ውጤት ለተቀረው ዓለም ብዙ ተስፋ ስለሚኖረው ነው።

ሳይንቲስቶች እስራኤል ላይ ዓይናቸውን የጣሉበት አንዱ ምክንያትም ይኸው ነው። አንድ ሕዝብ ሙሉ በሙሉ ክትባት ሲከተብ በዚያች አገር ተህዋሲው ምን ሊሆን ይችላል የሚለው አጓጉቷቸዋል።

ይህንን የክትባቱን ዘመቻ እያስተባበሩ ከሚገኙት ዋናው ሰው የፋይዘር ክትባት እንደተባለው ፍቱን ስለመሆኑ እርግጠኛ አይደለሁም በሚል ጥርጣሬ እንደገባቸው በይፋ ተናግረዋል።

ይህን እንዲሉ ያደረጋቸው ታዲያ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች የፋይዘር ክትባትን ከወሰዱ በኋላም ተህዋሲው ስለተገኘባቸው ነው።

ጥርጣሬው መፈጠር የጀመረውም አንድም በዚህ የተነሳ ነው። ሌሎች ሳይንቲስቶች ግን በጉዳዩ ላይ አስተያየት ለመስጠት ጊዜው ገና ነው ይላሉ።

እኚህ በክትባቱ ላይ ጥርጣሬን ያነሱት ፕሮፌሰር ናችማን አሽ በጤና ጥበቃ ሚኒስትር ጥርጣሪያቸው ውድቅ ተደርጎባቸዋል።

"የፕሮፌሰሩ አስተያየት ከአውድ ውጭ የተነገረና ትክክል ያልሆነ ነው" ብሏል የእስራኤል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ።

"በጽኑ የሚታመሙ ዜጎቻችን ቁጥር መቀነስ አለበት ብለዋል ፕሮፌሰሩ፣ ገና 2ኛው ዙር ብልቃጥ በመሰጠት ላይ ያለው አሁን ስለሆነ ይህ ውጤቱ በቀጣይነት የሚታይ እንጂ አሁን ምንም ማለት የሚቻልበት ደረጃ ላይ አይደለንም" ብሏል ይኸው መግለጫው።

እርግጥ ነው ክትባቱ የራሱ ባህሪ አለው።

አንድ ሰው ክትባት ከወሰደ በኋላ ሰውነቱ የተህዋሲውን ጄኔቲክ አውቆ ወራሪ ኃይል እንደመጣ ተገንዝቦ ለዚህ የሚሆን መከላከያ ለማዘጋጀት ጊዜ ይፈልጋል።

አንቲቦዲና ቲ'ሴል አምርቶ ተህዋሲውን ለመጋፈጥ ጊዜ ይፈልጋል። ይህ እስኪሆን የተከተበ ሰውም ቢሆን ሊታመም ይችላል። ቢመረመር ተህዋሲው ሊገኝበት ይችላል።

ይህ ሂደት ታዲያ እስከ 2 ሳምንት ሊወስድ እንደሚችል ፕሮፌሰር ዳኔ አልትማን፣ የኢምፔሪያል ኮሌጅ ለንደን ኢሚኑሎጂስት ይናገራሉ።

ክላት በእስራኤል ትልቁ የጤና ሽፋን ሰጪ ድርጅት ነው።

ይህ ድርጅት በቅርቡ ባወጣው መረጃ መሰረት ከተከተቡ 200 ሺህ፣ እድሜያቸው ከ60 በላይ የሆኑት ውስጥ በዚሁ እድሜ ላይ ያሉ ክትባቱን ግን ካልወሰዱ ሰዎች ጋር በማወዳደር በሰራው ጥናት በሁለት ሳምንት ውስጥ የተከተቡትም ያልተከተቡትም ላይ ተመጣጣኝ ቁጥር ያለው ሰው በተህዋሲው መያዙን ይፋ አድርጓል።

ይህ ነው በፋይዘር ክትባት ላይ ጥርጣሬ እንዲነግስ ምክንያት የሆነው።

ከዚያ በኋላ ቆይቶ ግን የተከተቡት ካልተከተቡት በ33 ከመቶ ባነሰ በተህዋሲው መያዛቸው እየተስተዋለ መምጣቱ ተነግሯል።

"ይህ ገና ጅምር ላይ ያለ የጥናት ውጤት ነው፤ በዚህ ደረጃ ራሱ በ33 በመቶ የተህዋሲው መዛመት ቀንሷል። ስለዚህ የሚያሳስብ ነገር የለም" ብለዋል የክላት ድርጅት የጤና መኮንን ራን ባሊቸር።

በፋይዘር የክሊኒክ የሙከራ ጊዜም ቢሆን ተመሳሳይ ነገር ታይቷል።

ክትባቱን በወሰዱና ባልወሰዱት መሀል በተደረገ ጥናት ግልጽ ልዩነት ለማየትና የመዛመት ፍጥነት ሲቀንስ ለመታዘብ 100 ቀናት ያስፈልጋሉ ነው የሚለው መድኃኒት አምራቹ ፋይዘር።

እስራኤል ዜጎቿን መከተብ የጀመረችው በታህሣሥ 19 ነበር።

አሁን የሕዝቧን 10 ከመቶ ከከተበች 2 ሳምንት አልፏታል።

ዛሬ ላይ ደግሞ ከ9 ሚሊዮን ሕዝቧ ውስጥ ግማሽ ሚሊዮኑ ክትባት ደርሶታል።

ነገር ግን በአገሪቱ ውስጥ በተህዋሲው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መቀነስ በጉልህ አልታየም። ለምን?

ክትባት የወሰደ ሰው የመከላከል አቅም ለማዳበር ከሚወስድበት ጊዜ አንጻር ቢያንስ ለአንድ ወራት ያህል ክትባቱ ያመጣውን ለውጥ ለማወቅ ከባድ ይሆናል ተብሏል።

ፕሮፌሰር ባሊቸር ግን በሚቀጥሉት ሳምንታት ውስጥ ወደ ጽኑ ሕሙማን የሚሄዱ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣት አለበት ይላሉ።

ፋይዘር መድኃኒት አምራች ሁለት ጠብታ ክትባቱን የወሰደ ሰው 95% በተህዋሲው ያለመያዝ እድሉ የሰፋ ነው ይላል።

ነገር ግን በብዙ ክትባቶች እንደታየው ከዚህ ያነሰ መቶኛ እንኳ የፈውስ እድል ብዙ ለውጥ ያመጣል።

አመታዊው የፍሉ ክትባት ለምሳሌ ፈዋሽነቱ ከ40-60% ብቻ ነው።

ሆኖም በየዓመቱ በሺ የሚቆጠሩ ሰዎችን ከሞት ይታደጋል።

አንዱ አሁን እያነጋገረ ያለው አንድ ጠብታ የወሰዱ ዜጎችን ሁለተኛውን ጠብታ እየሰጡ ቀስ በቀስ ሕዝቡን ማዳረስ ነው ወይስ አንዱን ጠብታ ለሰፊው ሕዝብ ካዳረሱ በኋላ ለ2ኛው ዙር እንደገና መጀመር ይሻላል የሚለው ነው።

ታላቋ ብሪታኒያ እንዳመነችው ብዙ ሰዎችን የመጀመርያውን ጠብታ ካዳረሱ በኋላ ለ2ኛው መመለስ ይሻላል የሚል ነው።

በዚህ ዘዴ በተህዋሲው የሚጋለጡ ሰዎችን ቁጥር መቀነስ ይቻላል ብላ አምናለች።

ትንሽ ቁጥር ያለውን ሕዝብ 2 ጠብታ ሰጥቶ ትንሽ ቁጥር ያለውን ሕዝብ ከተህዋሲው በደንብ መከላከል የተሻለ ነው የሚሉም አሉ።

ጠብታው መሰጠት ያለበት በ2 ሳምንት ልዩነት መሆኑም ሌላው ፈተና ነው። ምክንያቱም አንድ ሰው አንድ ጠብታ ከወሰደ በኋላ ሌላ ሁለት ሳምንት መጠበቅ ተህዋሲው ከጋረጠው ፈተና አንጻር ትእግስትን የሚፈታተን በመሆኑ ነው።

ፕሮፌሰር ኢቫንስ ማጠቃለያ ሐሳብ ሲሰጡ ይህን ይላሉ፡

"ከእስራኤል አሁን የሚመጡ ሪፖርቶች ያልተሟሉ ብቻ ሳይሆን መረጃን የሚሰጡ፥ እንዲሁም አጥጋቢ ሆነው አላገኘናቸውም። በታላቋ ብሪታኒያ ሁለተኛውን ጠብታ አዘግይቶ የመጀመርያውን ጠብታ ማዳረስ የሚለውን አሰራር ሊያስቀይር የሚችል ነገርም አላገኘንባቸውም"

ዞሮ ዞሮ በቀጣይ ወራት በእስራኤል ተህዋሲው ድራሹ እየጠፋ ካልመጣ ዓለም መደንገጡ አይቀርም።