ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የቻይናው ሚኒስትር ጭምብል ባለማድረጋቸው በታንዛኒያው ፕሬዝዳንት ተመሰገኑ
የታንዛኒያው ፕሬዝዳንት ጆን ማጉፉሊ ለጉብኝት ወደ አገራቸው የመጡት የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ባለማድረጋቸው ምሰጋና አቀረቡ።
ፕሬዝዳንቱ ይህ አጋጣሚም በአገራቸው የኮሮናቫይረስ አለመኖሩን የሚያረጋግጥ ማሳያ እንደሆነም ተናግረዋል።
"ሚኒስተር ዋንግ ታንዛኒያ ውስጥ ኮሮናቫይረስ እንደሌለ አውቀው ጭምብል ባለማድረጋቸው ላመሰግናቸው እወዳለሁ። በጣም አመሰግናለሁ" ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።
ማጉፉሊ ካቀረቡት ምስጋና በተጨማሪም "ይህንንም ለማረጋገጥ አንድ ላይ ምግብ ለመመገብ በምንሄድበት ጊዜ በመጨባበጥ ይህንን አረጋግጣለሁ" ሲሉም ተናግረዋል።
በእርግጥም የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ አብረዋቸው ወደ ታንዛኒያ ከተጓዙት የቡድናቸው አባላት በተለየ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ባለማድረግ ለየት ብለው ታይተዋል።
የታንዛኒያው ፕሬዝዳንት ጆን ማጉፉሉ በዓለም የጤና ድርጅት የኮሮናቫይረስ መስፋፋትን ለመግታት ያግዛሉ ብሎ ተግባራዊ እንዲሆኑ ካዘዛቸው መመሪያዎች መካከል አካላዊ ርቀትን መጠበቅን የመሳሰሉ እርምጃዎችን በማጣጣልና በአገሪቱ ያለውን የወረርሽኝ ሁኔታን በተመለከተ በሰጡት ዝቅ ያለ ትኩረት ሳቢያ ጠንካራ ትችት ሲሰነዘርባቸው ቆይቷል።
ታንዛኒያ ከሌሎቹ የአፍሪካ አገራት በተለየ በአገሯ ስላለው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ዙሪያ መረጃ ማውጣት ካቆመች ረጅም ጊዜ ሆኗታል። በዚህም በታንዛኒያ በበሽታው የሞቱና የተያዙ ሰዎች አሃዝ በትክክል አይታወቅም።
የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ታንዛኒያን ጨምሮ በናይጄሪያ፣ በዲሞክራቲክ ኮንጎ፣ በቦትስዋናና በሲሸልስ የአምስት ቀናት ጉብኝት ለመድረግ ነው ወደ አፍሪካ የመጡት።
በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት መጀመሪያ ላይ ከአፍሪካ አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯን የላከችው ቻይና "የሕክምና ባለሙያዎችን እንደምትልክ" ከውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቷ የወጣው መረጃ አመልክቷል።
በተጨማሪም በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሰበብ የተጓተቱ የግንባታ ሥራዎችን በማፋጠን ለማጠናቀቅ ጥረት እንደሚደረግ ተገልጿል።
የሚኒስትሩ ጉብኝት የአፍሪካ ጉብኝት በቻይናና በአህጉሪቱ ሕዝቦች መካከል መቀራረብን በመፍጠር የጋራ የወደፊት ግብን መፍጠር መሆኑም ተገልጿል።