የአሜሪካ ምርጫ 2020 ፡ በጆርጂያ ለሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ምርጫ ለመጀመርያ ጊዜ ጥቁር እንደራሴ 'አሸነፉ'

ዲሞክራቶችና ሪፐብሊካኖች የሞት ሽረት ትግል እያደረጉ ባሉበት ደቡባዊ የአሜሪካ ግዛት ጆርጂያ ራፋኤል ዋርኖክ ድል ቀንቷቸዋል እየተባለ ነው።

ዩኤስ ቲቪ እና አሶሺየትድ ፕሬስ የዜና ወኪል ራፋኤል ማሸነፋቸውን ይፋ አድርገዋል።

ቆጠራው ለጊዜው መቶ በመቶ ባይጠናቀቅም ከ98 ከመቶ በላይ ድምጽ ተቆጥሮ ነው ራፋኤል ዋርኖክ አሸንፈዋል የሚለው መረጃ እየወጣ ያለው።

ይህ መረጃ ከተረጋገጠ ራፌኤል ዋርኖክ ቀድሞ ባሪያ አሳዳሪ ከነበረችው ጆርጂያ ግዛት በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ግዛቷን የሚወክል ጥቁር ሰው ሆነው የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ሸንጎን ይቀላቀላሉ።

ዋርኖክ ያሸነፉት ባለጸጋዋን የቀድሞዋን የሴኔት አባል ኬሊ ሊዮፍለርን በትንሽ ልዩነት በልጠው ነው ተብሏል።

ይህ በጆርጂያ ግዛት እየተደገ ያለው ምርጫ የድጋሚ ምርጫ ሲሆን የድጋሚ ምርጫ እንዲካሄድ የተወሰነው ባለፈው ኅዳር አንድም እጩ 50 ከመቶ የመራጭ ድምጽ ባለማግኘቱ ነው።

በግዛቲቱ የምርጫ ሕግና ደንብ መሰረት ተወዳዳሪ እጩዎች በምርጫ ከ50 ከመቶ በላይ ካላስቆጠሩ ለ2ኛ ዙር ድምጽ እንዲሰጥ ያዛል።

በአሜሪካ ታሪክ አንድ ግዛት መላውን የአሜሪካ እጣ ፈንታ ሊወስን የሚችልበት አጋጣሚ ሲፈጠር ጆርጂያ ግዛት ምናልባትም የመጀመርያዋ ሳትሆን አትቀርም ይላሉ ተንታኞች።

ምክንያቱም በአሜሪካ የመንግሥት አስተዳደር የሕግ መወሰኛ ምክር ቤትን የበላይነት መያዝ እጅግ ቁልፍ ጉዳይ በመሆኑ ነው።

አሁን የበላይነቱን ዲሞክራቶች ለመያዝ የሚችሉት በጆርጂያ ራፋኤል ዋርኖክን ጨምሮ ሌላኛው የዲሞክራቲክ ዕጩም ካሸነፉ ብቻ ነው።

ዋርኖክና ኬሊ ሎፍለር እጅግ ፈታኝ ውድድር ያደረጉ ሲሆን ዋርኖክ 50.5 በመቶ በማግኘት ኬሊን አሸንፈዋታል ነው የሚሉት፣ አሁን እየወጡ ያሉ መረጃዎች።

ይህ ጊዜያዊ ውጤት ይፋ የሆነው እስከ አሁን 98 ከመቶ የሚሆነው የመራጮች ድምጽ ከተቆጠረ በኋላ ነው።

አሁን በጉጉት እየተጠበቀ ያለው የዲሞክራቱ ጆን ኦሶፍ እና የሪፐብሊካኑ ዴቪድ ፐርዲዮ የፖለቲካ ፍልሚያ ውጤት ነው።

ከሁለቱ ዕጩዎች ማን አሸናፊ ነው የሚለውን ለመለየት ቆጠራው ቀጥሏል። በጣም የተቀራረበ ድምጽ እያገኙ ስለሆነ ግን ይህ ዘገባ እስከሚጠናቀርበት ሰዓት ድረስ አሸናፊውን መለየት አልተቻለም።

የ51 ዓመቱ ራፋኤል ዋርኖክ ጆርጂያ አትላንታ ውስጥ ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየር ድሮ በሰባኪነት የሰራበት የኤቤኔዘር ቤተክርስቲያን ሰባኪ ሲሆን እንደ ማርቲን ሉተር ኪንግ ሁሉ ለጥቁሮች መብት ድምጹ በማሰማት ይታወቃሉ።

ዛሬ ጆርጂያን አንድ ጥቁር በሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ሊወክላት መቻሉ ትልቅ ፈንጠዚያን በዲሞክራቶች ዘንድ ፈጥሯል።

ራፋኤል ዋርኖክ የድሉን መታሰቢያ ለእናቱ ቬርሌኒ አድርጎታል። እናቱ ቬርለኒ በጆርጂያ ግዛት ገና በአፍላነታቸው በእርሻ ውስጥ የጉልበት ሠራተኛ ሆነው አስቸጋሪ ልጅነትን ያሳለፉ ናቸው።

"ይህ አሜሪካ ስለሆነ በአንድ ወቅት ጥጥ ለቃሚ የነበሩ የእናቴ እጆች ለትንሹ ልጃቸው ድምጽ ሊሰጡ ምርጫ ጣቢያ ተገኙ" ሲል የ82 ዓመት እናቱን አሞካሽቷል።

"ወደ ምክር ቤቱ የምገባው ለሁሉም የጆርጂያ ነዋሪ ለመሟገት ነው ብሏል ዋርኖክ ውጤቱን ተከትሎ። "ለእኔ ድምጽ የሰጣችሁኝም፣ ያልሰጣችሁኝም በእኔ ዘንድ እኩል ናቸው። ለናንተ ነው የምታገለው" ብሏል ራፋኤል ዋርኖክ።

ዶናልድ ትራምፕ በዚህ ግዛት ተገኝተው የምርጫ ቅስቀሳ ሲያደርጉ ለጆርጂያዊያን ይህ ምርጫ የሪፐብሊካን የመጨረሻው የጦር ግንባር ነው ሲሉ ነበር የተናገሩት።

ይህን ያሉበት ምክንያት እንደተፈራው ዲሞክራቶች በጆርጂያ 2 ዕጩዎቻቸው ከተመረጡ በሕግ መወሰኛው ምክር ቤት የሚኖራቸው የወኪል ብዛት 50 ይሆናል። ይህም ከሪፐብሊካን እንደራሴዎች ጋር እኩል ያደርጋቸዋል።

ክርክር በሚደረግ ጊዜ ሴኔቱን በሊቀመንበርነት የሚመሩት ካምላ ሐሪስ ስለሚሆኑ ሁልጊዜም ዲሞክራቶች ያሉት ነገር እንዲሆን ሰፊ እድል ይሰጣቸዋል።

በአሁኑ ጊዜ የሕግ መወሰኛው ምክር ቤት በሪፐብሊካን እንደራሴዎች የበላይነት የተያዘ ነው።

የታችኛው ምክር ቤት ደግሞ በዲሞክራቶች የበላይነት ይዘወራል።

የራፋኤል ዋርኖክ ማሸነፍ ብቻውን ግን የዲሞክራቶችን በሴኔት የበላይነት አያስገኝም። ጆን ኦሶፍ ሪፐብሊካኑን ዕጩ ዴቪድ ፐርዲዮን ማሸነፍ ይኖርባቸዋል።

ውጤቱ በጥቂት ሰዓታት ሊታወቅ ይችላል እየተባለ ነው።