የሕዝብ እንደራሴዎች ትራምፕ በወንጀል እንዲከሰሱ ደብዳቤ ጻፉ

የጆርጂያ ግዛት የምርጫ አስፈጻሚ የሆኑት ብራድ ራፈንስበርገር ትራምፕ ስልክ ደውለው 'እንዳሸንፍ የሚያበቃኝን የመራጮች ድምጽ ከየትም ውለድ' ማለታቸው "አሳፋሪ ስህተት ነው' ሲሉ ተናገሩ።

ብራድ ይህን አስተያየት የሰጡት በእሳቸውና በፕሬዝዳንቱ መካከል የተደረገው የስልክ ልውውጥ ድምጽ በዋሺንግተን ፖስት ጋዜጣ መጋለጡን ተከትሎ ነው።

ትራምፕ ግለሰቡን ስልክ ደውልው ቁም ስቅላቸውን ሲያሳይዋቸው የሚያስደምጠው የድምጽ ቅጂ ይፋ ከሆነ ወዲህ በተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ላይ ውግዘት በርትቷል።

አንዳንዳንዶች እንዲያውም "የፕሬዝዳንቱ ድርጊት በወንጀል የሚያስጠይቅ ነው" እስከማለት ደርሰዋል። ሁለት ሕግ አዋቂ የታችኛው ምክር ቤት አባላትም ለአሜሪካ ወንጀል ምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ) ፕሬዝዳንቱ ላይ የወንጀል ዶሴ እንዲከፈትባቸው የሚጠይቅ ደብዳቤ ጽፈዋል።

ዶናልድ ትራምፕ ከጆ ባይደን ጋር ለፕሬዝዳንትነት ሲፎካከሩ በጆርጂያ ግዛት በጠባብ ልዩነት ነበር የተሸነፉት።

ይህን ለማስቀልበስ ነበር የምርጫ አስፈጻሚው ጋር ፕሬዝዳንቱ በግል ደውለው "ትንሽ ድምጽ ብትፈልጉልኝ ምናለበት" እያሉ ሲያባብሉ የነበረው።

የትራምፕ ወዳጆች የሆኑት የሪፐብሊካን ፓርቲ ባለሥልጣናት የፕሬዝዳንቱ ቅሌት በዚህ ሰዓት ይፋ መደረጉ በጆርጂያ አሁን የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት መቀመጫ ለማግኘት ለሚደረገው ወሳኝ ምርጫ የትራምፕ ድርጊት በሪፐብሊካኑ እጩ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ሊፈጥር ይችላል በሚል ስጋት ገብቷቸዋል።

ለሕግ መወሰኛው ምክር ቤት እንደራሴነት ዛሬ በጆርጂያ በሚደረገው ምርጫ ዲሞክራቶች ካሸነፉ የላዕላይ ምክር ቤቱን በበላይነት ለመቆጣጠር ስለሚያስችላቸው ለጆ ባይደንና ለካምላ ሐሪስ ሠርግና ምላሽ ይሆንላቸዋል ተብሏል።

ምክንያቱም ዲሞክራቶች ናንሲ ፒሎሲ የሚመሩትን የሕግ መምሪያውን ምክር ቤት የበላይነት የተቆጣጠሩ ሲሆን አሁን በጆርጂያ በለስ ከቀናቸው ደግሞ የላዕላይ ምክር ቤቱ በዲሞክራቶች ቁጥጥር ይወድቃል። ይህም ጆ ባይደን ያለምንም ፈተና ፖሊሲዎቻቸውን እንዲያስፈጽሙ ያግዛቸዋል።

የጆርጂያ ምርጫ ላይ ዲሞክራቶች ቢያሸንፉ ከሪፐብሊካን ጋር በውክልና እኩል ቁጥር ያገኛሉ። ሆኖም የሕግ መወሰኛው ምክር ቤት የሚመራው በምክትል ፕሬዝዳንት ስለሆነ ካምላ ሐሪስ የሚኖራቸው ድምጽ ወሳኝ ሆኖ ይቀጥላል ማለት ነው።

በትራምፕ ዘመን የላዕላይ ምክር ቤቱ በሪፐብሊካን አብላጫ መያዙ ለዲሞክራቶች ራስ ምታት ሆኖ እንደቆየባቸው ይታወቃል።

የጆርጂያ ምርጫ አስፈጻሚ ብራድ ከኤቢሲ ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በወቅቱ ፕሬዝዳንቱ እየደወሉ ሲያባብሏቸው ብዙውን ጊዜ ፕሬዝዳንቱ ተናጋሪ እሳቸው ደግሞ አድማጭ ሆነው ለሰዓታት እንደሚቆይ ተናግረዋል።

ሆኖም ግን "ፕሬዝዳንቱ እየተናገሩ ያሉት ነገር ስህተት እንደነበረ በተደጋጋሚ ነግሪያቸዋለሁ" ብለዋል ብራድ።

ዋሺንግተን ፖስት ይፋ ያደረገው የስልክ ቅጂ እሳቸውና ፕሬዝዳንቱ ቢያንስ ለአንድ ሰዓት ያህል ሲነታረኩ የሚያስደምጥ ነው።

የትራምፕ ጥያቄ በግዛቲቱ ውስጥ ምርጫው ተጨበርብሯል በሚል ለማሸነፍ የጎደሏቸውን ድምጾች ከየትም ብሎ ፈልገው እንዲሞሉ የሚወተውቱ ነበሩ።

ብራድ ለኤቢሲ እንተናገሩት ይህ የስልክ ልውውጥ እየተቀዳ እንደሆነ በወቅቱ መረጃ አልነበራቸውም።

"ዶናልድ ትራምፕ ይሉኝ የነበረው በሺዎች የሚቆጠሩ የሞቱ ሰዎች ድምጽ ሰጥተዋል (በፖስታ ድምጽ ሰጥተው ሕይወታቸው ያለፈ) ነው። እኔ ደግሞ ያገኘሁት ሁለት ሰዎችን ብቻ ነው። በዚህ ደረጃ ፕሬዝዳንቱ በስህተት ተነክረው ነበር" ብለዋል።

ዶናልድ ትራምፕ በስልክ ልውውጡ ወቅት ብራድ የተወሰኑ ድምጾችን ከዚያም ከዚህም ብለው ቢያገኙላቸው እሳቸው ግዛቲቱን አሸንፈው ለሌላ 4 ዓመት የአሜሪካ ፕሬዝዳንት እንደሚሆኑ ይናገራሉ።

ዶናልድ ትራምፕ ሰውየውን አንዳንዴ በማባበል፣ ሌላ ጊዜ በማስፈራራት ሊያግባቧቸው ሲሞክሩ በቀጭኑ ሽቦ ይሰማል።

የሪፐብሊካን ፓርቲ አባል የሆኑት የምርጫ አስፈጻሚው ብራድ ግን በእርጋታ ፕሬዝዳንቱ የሚሉት አሐዝ የተሳሳተ እንደሆነ ሲነግሯቸው ይሰማል።

"የእስርዎ ችግር ክቡር ፕሬዝዳንት! የተሳሳተ መረጃ ይዘው መውጣትዎ ነው" ሲሏቸውም ይደመጣል።

የዚህን የስልክ የድምጽ ልውውጥ ሾልኮ መውጣትን ተከትሎ ፕሬዝዳንቱ በወንጀል መጠየቅ የለባቸውም ወይ የሚሉ አስተያየቶች ሚዲያውን ሞልተውታል።

ሁለቱ የታችኛው ምክር ቤት አባላትን ለኤፍቢአይ ደብዳቤ የጻፉት ይህን ተከትሎ ነበር።

ደብዳቤው ኤፍ ቢ አይ በትራምፕ ላይ የወንጀል ምርመራ እንዲጀምር የሚጠይቅ ነው።

ጆርጂያ የሚገኙት ተመራጭ ምክትል ፕሬዝዳንት ካምላ ሐሪስ በበኩላቸው የትራምፕን ድርጊት በሥልጣን መባለግ ነው ሲሉ ገልጸውታል።

የሴኔት ተጠሪ ዲክ ደርቢን በበኩላቸው የትራምፕን ድርጊት አደገኛ ብለውታል።

የትራምፕ ድርጊት በጆርጂያ ምርጫ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል ወይ የሚለው የፖለቲካ አዋቂዎችን እያከራከረ ነው።

ጆ ባይደንም ሆኑ ካምላ ሐሪስ ከትናንት ጀምሮ በጆርጂያ የዲሞክራቲክ እጩ እንዲያሸንፍላቸው ቅስቀሳ በማድረግ ተጠምደው ነው የዋሉት።

ጆ ባይደን በአትላንታ ተገኝተው መራጮች ለዲሞክራቲክ እጩ ድምጽ እንዲሰጡና ታሪክ እንዲሰሩ ተማጽነዋል።

ትራምፕ በበኩላቸው የጆርጂያ መራጮች በፍጹም ዲሞክራት እጩ እንዳይመርጡ አስጠንቅቀዋል።

"ዲሞክራቶች የታችኛውንም የላይኛውንም ምክር ቤት ከተቆጣጠሩ አደገኛ ነው። ልንታገላቸው ይገባል" ብለዋል። አክለውም፤ ይህ የምትሰጡት ድምጽ በሕይወት ዘመናችሁ ሁሉ ከምትሰጡት ድምጽ እጅግ ወሳኙ እንደሆነ ልነግራችሁ እወዳለሁ ብለዋል።

ጆርጂያ በሕግ መወሰኛው ምክር ቤት እንደራሴ የነበሩት ሪፐብሊካኑ ሴናተር ዴቪድ ፐርዱ ውክልናቸውን ለማስጠበቅ ነው የሚታገሉት።

የዲሞክራቱ እጩ ጆን ኦሶፍ የትራምፕን ድርጊት የዲሞክራሲ ጸር ሲሉ ኮንነውታል።