ቴክኖሎጂ፡ የ12 ዓመቷ ታዳጊ ቲክቶክን ልትከስ ነው

የ12 ዓመቷ ታዳጊ ቲክ ቶክን ልትከስ ነው።

ታዳጊዋ ተንቀሳቃሽ ምስልን የሚያጋራውን መተግበሪያ፣ ቲክቶክን የምትከስሰው የሕጻናትን ዳታ [መረጃ] ከሕግ ውጪ ተጠቅሟል በሚል ነው ተብሏል።

ፍርድ ቤቱ ክሱ የሚታይ ከሆነ የታዳጊዋን ማንነት ለመደበቅ ተስማምቷል።

ጉዳዩ በእንግሊዝ የሕጻናት ኮሚሽነር አኔ ሎንግፊልድ ድጋፍን አግኝቷል።

ኮሚሽነሯ ቲክቶክ የዩናይትድ ኪንግደምን እንዲሁም የአውሮፓን የዳታ ሕግ ጥሷል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

ቲክቶክ በበኩሉ የሕጻናትን ደኅንነት ለመከላከል "ፖሊሲዎቹን ማሸሻሻሉን" ጠቅሶ፣ እድሜያቸው ከ13 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች መተግበሪያውን መቀላቀል እንደማይችሉ ተናግሯል።

ኮሚሽነር ሎንግፊልድ ይህ ጉዳይ እድሜያቸው ከ16 በታች ለሆኑ የቲክቶክ ተጠቃሚዎች በእንግሊዝ እንዲሁም ከተቻለ በሌሎች አገራት የተሻለ ጥበቃ ማድረግ ያስችላል ብለዋል።

ኮሚሽነሯ የተንቀሳቃሽ ምስል ማጋሪያ መተግበሪያው የሕጻናት ግላዊ መረጃን በመሰብሰብ አልጎሪዝሙ ቪዲዮዎችን እንዲገፋ በማድረግ፣ የተመልካቾችን ቀልብ ለመሳብ እንዲሁም የማስታወቂያ ገበያ ለማግኘት እንደሚጠቀምበት ተናግረዋል።

ኮሚሽነር ሎንግፊልድ ለለንደን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በቪዲዮ እንደተናገሩት ይህ ጉዳዩ መተግበሪያው የሕጻናትን ግላዊ መረጃ እንዲሰርዝ በማድረግ ለሌሎች ምሳሌ እንደሚሆን ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል።

ነገር ግን በቅድሚያ ፍርድ ቤቱ የ12 ዓመቷ ታዳጊ ማንነቷ ተደብቆ ጉዳዩ ሊታይ ይችላል አይችልም የሚለው ላይ ለመወሰን ውሳኔ መስጠት አለበት ተብሏል።

ዳኛው የታዳጊዋ ማንነት ይፋ ከሆነ ለማኅበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎች ማንጓጠጥና ስድብ ልትጋለጥ ትችላለች ሲሉ ተናግረዋል።

አክለውም ማንነቷ ከታወቀ "በዚህ ጉዳይ ምክንያት ያላቸው የማኅበራዊ መገናኛ ብዙሃን ጥቅም እና ሌሎች ጉዳዩች አደጋ ላይ ይወድቃል ብለው የሚያምኑ ተጠቃሚዎች ያልተገባ ነገር ሊያደርጉ ይችላሉ" ሲሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል።

ኮሚሽነሯ ቲክቶክን ከመክሰሳቸው በፊት ጎግል ላይ የተመሰረተው የግላዊ መረጃ መከላከል ክስ እስኪጠናቀቅ መጠበቅ ይፈልጋሉ።

ቲክቶክ በሕጻናት መራጃ አያያዝ በ2019 በአሜሪካ የፌደራል የንግድ ኮሚሽን ተከስሶ፣ የ5.7 ሚሊዮን ዶላር ቅጣት ተጥሎበት ነበር።

መተግበሪያው በ2020 በደቡብ ኮሪያም በተመሳሳይ ጉዳይ ቅጣት ተጥሎበታል።

ቲክቶክ በበኩሉ ባወጣው መግለጫ፣ "እኛ ለደኅንነት እና ለግለሰቦች መብት ቅድሚያ እንሰጣለን፤ ለዚህም ሁሉንም ተጠቃሚዎቻችንን ለመከላከል የሚያስችል፣ ቴክኖሎጂያችንን፣ ፖሊሲያችንን አሻሽለናል፤ በይበልጥ ደግሞ ወጣት ተጠቃሚዎችን መከላከል የሚያስችል የፖሊሲ ማሻሻያዎችን አድርገናል" ብሏል።

መተግበሪያው እድሜያቸው ከ13 ዓመት በታች ለሆኑ ቲክቶክ መጠቀምን አይፈቅድም።

እነዚህ ታዳጊዎች አካውንት ከፍተው ከተገኙም ድርጅቱ እየተከታተለ አካውንታቸውን ይሰርዛል።