'በቆዳ ቀለሜ ምክንያት እንክብካቤ ተነፈገኝ' ያለችው ሀኪም በኮቪድ-19 ሞተች

በአሜሪካዋ ኢንዲያና የምትገኝ አንዲት ጥቁር አሜሪካዊት የሕክምና ባለሙያ በኮቪድ-19 ምክንያት ሕይወቷ አልፋል።

ባለሙያዋ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ሆስፒታል ብትገባም በቆዳ ቀለሟ ምክንያት ዶክተሮች ተገቢ እንክብካቤ እንዳላደረጉላት ስትናገር ቆይታለች።

ሱዛን ሙር የተሰኘችው ሐኪም ከኢንዲያና ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ውስጥ በለቀቀችው ቪድዮ ላይ እንክብካቤ ለማግኘት ዶክተሮችን 'ትለምን' እንደነበር ትናገራለች።

ሆስፒታሉ በሞቷ የተሰማውን ሃዘን ገልጿል።

ዩኒቨርሲቲው የቀረበበትን ክስ እንደሚመለክትም ተናግሯል።

ጥናቶች እንደሚያመለከቱት ጥቁሮች ከነጮች የበለጠ በኮሮናቫይረስ ምክንያት የመሞት ዕድላቸው የሰፋ ነው።

የ52 ዓመቷ ዶክተር ሙር ባለፈው እሁድ አንድ ሌላ ሆስፒታል ውስጥ ሳለች ነው ሕይወቷ ያለፈው።

በያዝነው ወር መጀመሪያ አካባቢ ነበር በፌስቡክ ገጿ መልዕክቷን ያስተላለፈችው።

ምንም እንኳ እያለቀሰችና ትንፋሽ እያጠራት ቢሆንም ነጭ ነው ያለችው ዶክተር ምን ያክል ሕመሟን አንደሚያጣጥል በቪድዮ መልዕክቷ ትናገራለች።

"ሳንባዬን አላደመጠውም፣ በፍፁም ሊነካኝ ፈቃደኛ አልነበረም፣ ምንም ዓይነት አካላዊ ምርመራ አላደረገለኝም። ምን እንደሚሰማኝ ልትነግረኝ አትችልም ስል ነግሬው ነበር" ትላለች።

ሆስፒታሉ 'ዘርን መሠረት ያደረገ እንክብካቤ መንፈግ እንደማይፈቅድ' አስታውቆ 'በቀረበው ክስ ላይ ምርመራ እንደሚያከናውን' በኦፌሴላዊ ምላሹ አስታውቋል።

የመርሳት በሽታ ያለባቸው የዶክተሯ ወላጆችና የ19 ዓመት ወንድ ልጇ ከዩኒቨርሲቲ ሆስፔታሉ ወደ ሌላ ሆስፒታል እንድትዘዋወር ቢያደርጓትም ልትተርፍ አልቻለችም።

የዶክተሯን ቤተሰቦች ወጭ ለመሸፈን የተቋቋመቀወ 'ጎፈንድሚ' የተሰኘው የበይነ መረብ ገንዘብ መሰብሰቢያ አስካሁን ድረስ 102 ሺህ ዶላር ተዋጥቶበታል።

ዶክተር ሙር ኮቪድ-19 ከያዛት በኋላ ከፍተኛ ትኩሳትና የመተንፈስ ችግር አጋጥሟት ነበር።

የሕክምና ባለሙያ በመሆኗ ተገቢው መድኃኒትና እንክብካቤ እንዲሰጣት ብትጠይቅም ዶክተሯ ለዚህ ሕክምና እንደማትመጥን በመናገር ወደ ቤት እንድትሄድ ነግሯት ነበር።

"የሕክምና ባለሙያ እንደሆንኩ ያውቃል። የመድኃኒት ሱስ የለብኝም። እጅጉን እያመመኝ ነበር" ብላለች በመልዕክቷ።

ዶክተር ሙር ከሆስታሉ ተገቢውን ሕክምና ሳታገኝ እንድትወጣ ከተደረገ በኋላ ባጋጠማት ሕመም ተመልሳ ገብታ ነበር።

"ሁሌም እለዋለሁ - ነጭ ብሆን ኖሮ ይሄ ሁሉ አይደርስብኝም ነበር።"

የዶክተሯ ሞት አሜሪካ ውስጥ ጥቁር አሜሪካዊያን ተገቢውን ሕክምና እንደማያገኙ የሚያሳይ ነው ያሉ ብዙዎች ድምፃቸውን በማሰማት ላይ ናቸው።

ጥቁር አሜሪካዊያን በኮሮናቫይረስ የመሞት ዕድላቸው ከነጭ አሜሪካዊያን በሶስት እጥፍ የላቀ ነው።