መቀመጫቸው የተቀደዱ የፒጃማ ማስታወቂያዎች ጉዳይ እያነጋገረ ነው

በተለያዩ የኢንተርኔት ገጾች ላይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያልተጠበቁ ማስታወቂያዎች ብቅ እያሉ ነው።

ከእነዚህ የሚበዙት የፒጃማ ሱሪዎች ሲሆኑ ልዩ የሚያደርጋቸው ደግሞ መቀመጫቸው አካባቢ መጣፊያ እንኳ ሳያበጁ ሽንቁር የተው መሆናቸው ነው።

ይህ ለብዙዎች አሳፋሪ፣ ለሌሎች የሳቅ ምንጭ ለአንዳንዶች ደግሞ ብልህ የማስታወቂያ ስልት ሆኖ እያነጋገረ ነው።

ፒጃማ አምራቾች በስፋት እያስተዋወቋቸው ያሉት እነዚህ የምሽት አልባሳት ለምን ይህንን የማስተዋወቅ ዘዴ ለመጠቀም ቻሉ የሚለው በስፋት አነጋግሯል።

በማኅበራዊ የትስስር ገጾች ነገሩ ትልቅ ክርክር አስነስቷል። ከባሕል፣ ከማስታወቂያ ሕግና ደንብ፣ ከንግድ እንዲሁም ከሸማቾች መብት አንጻር ጉዳዩ በስፋት እያነጋገረ ነው።

እነዚህ ማስታወቂያዎች ኢንተርኔት ላይ እንደ አሸን የፈሉት ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ነው።

አንዳንድ ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ለምን እነዚህ ማስታወቂያዎች እነሱን ዒላማ ሊያደርጉ እንደቻሉ አብዝተው ይጠይቃሉ።

ጉግል ማስታወቂያዎችን በኢንተርኔት ሲበትን ከአሳሹ ባህሪና የፍላጎት አዝማሚያ ጋር የሚቀራረቡትን መርጦ እንደሆነ ተለምዷዊ የአልጎሪዝም አሰራሩ ያሳያል።

አንድ የማስታወቂያ ባለሙያ ምናልባት እነዚህ መቀመጫ ላይ መጣፊያ እንኳ የሌላቸው የፒጃማ ማስታወቂያዎች ከኢንተርኔት ተጠቃሚዎች መረጃ ለመሰብሰብ የታለሙ ሊሆኑ እንደሚችሉ ገምተዋል።

እነዚህ መቀመጫቸው የተቦደሱ ፒጃማዎች በስፋት ሲተዋወቁ ነበር የተባለው አይቪሮዝ (IVRose) ለተሰኘው የንግድ ምርት መለያ (ብራንድ) ነው።

የአይቪሮዝ የፌስቡክ ገጽና ማስታወቂያ ክንፉ የሚተዳደረው ደግሞ ሻንጋይ ሊሻንግ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኮርፖሬሽን ሊሚትድ በተባለ የቻይና ድርጅት ነው።

ይህንን ፒጃማ እያስተዋወቁ ያሉ በርከት ያሉ የልብስ አምራች ድርጅቶች የማስታወቂያ ውክልናቸውን ለዚህ ድርጅት እንደሰጡ ይገመታል።

አልክማንድ ኢስቴት ሊሚትድ የሚያስተዳድራቸው በርካታ የልብስ አምራቾች ድረ ገጾች ይህንኑ ተመሳሳይ የፒጃማ ማስታወቂያን እያሰራጩት ይገኛሉ።

አሁን ጥያቄ የሆነው በዚህ መንገድ ማስታወቂያውን በገፍ ወደ ኢንተርኔት ዓለም መልቀቁ ለምን አስፈለገ? ዓላማውስ ምንድነው? የማስታወቂያ ደንብና ሥነ ምግባሩስ ይፈቅዳል ወይ? የሚለው ነው።

ዲጂታል ዊስኪ የተሰኘው ኩባንያ ማርኬቲንግ ዳይሬክተር ማት ሞሪሰን በዚህ ጉዳይ ላይ ለቢቢሲ የግል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

እሳቸው እንደሚሉት ወትሮም የቻይና ማስታወቂያ ድርጅቶች በአንድ ጊዜ አነጋጋሪ ሊሆኑ የሚችሉ፣ እንደ ወረርሽኝ የሚዛመቱ፣ አንዳንዴም ሰዎችን ሊያናደዱ የሚችሉ ከተለምዶ ወጣ ያሉ ማስታወቂያዎችን በመሥራት የታወቁ ናቸው።

በአንድ ጊዜ ኢንተርኔቱን ማጥለቅለቃቸው ደግሞ አስተዋዋቂዎቹ ምርቶቹ ለየትኛው አገር፣ በየትኛው እድሜና ፍላጎት ላይ ላለ የሚለውን ቅጽ ሲሞሉ ሁሉንም አካታች አድርገው በዘፈቀደ ስለሚሞሉት ነው ይህ የፒጃማ ማስታወቂያ ዓለምን ያጥለቀለቀው ብለዋል።

የተወሰነ ጾታና የዕድሜ ክልልን ዒላማ ማድረግ በማስታወቂያ ተፈላጊውን ውጤት በአጭር ጊዜ እንደሚያመጣ ይታመናል፤ ከማስታወቂያ በጀት አንጻርም የሚመከረው ይኽው አሰራር ነው።

ሆኖም በቻይና ማስታወቂያ ድርጅቶች ከዚህ የተለየ ዘዴን መጠቀም አዲስ አይደለም፤ ውጤትም አግኝተውበታል የሚሉ ባለሙያዎች አሉ።

ሚስተር ሞሪሰን እንደሚሉት የአንዳንድ ማስታወቂያዎች ግብ ምርቱን ማሻሻጥ ብቻ ነው ብሎ መደምደም ስህተት ነው ይላሉ።

አንዳንድ ጊዜ የሸማችን መረጃ ለመሰብሰብ፣ ምን ያህል ሰው በምን ዓይነት ጉዳይ ይማረካል የሚለውን ለማየት፣ ወይም ገሸሽ የተደረገን ምርት አነጋጋሪ አድርጎ ዳግም ከሞት ለማስነሳት ማስታወቂያዎች በገፍ ኢንተርኔት ላይ ሊፈሱ ይችላሉ ብለዋል።

የመቀመጫን ሸንቁር የሚያሳዩ ማስታወቂያዎች እንዴት የኢንተርኔት ደንብን ሊተላለፉ እንደቻሉ ሲያስረዱም ነገሩ በቀጭን ክር እንደመራመድ ነው ይላሉ።

የኢንተርኔት ማስታወቂያ አታሚዎችን ደንቦች ባለመተላለፍና ግን ደግሞ የሸማቾችን ሙሉ ትኩረት በማግኘት መሀል የተዘየደ ብልህ የማስታወቂያ ስልት ነው ይላሉ ሞሪሰን።

እርቃን ወጥተዋል እንዳይባሉ አይደሉም፣ ግን ደግሞ ለዓይን የሚስቡና አይረሴ ናቸው፣ ደግሞ አነጋጋሪ ሆነዋል፤ የሚፈለገውም ይኽው ነበር።

ምን ጊዜም ማስታወቂያ ሸማቾቹን በትንሹ ማስቆጣት አለበት፤ አለበለዚያ ትኩረት ይነፈገዋል።

አንድ ሰው በኢንተርኔት ማስታወቂያ ላይ ጥቁምታ (ክሊክ) ሲያደርግ ቀጥሎ በሚያደርገው የኢንተርኔት አሰሳ ተመሳሳይ ምርቶች ወደእሱ እንዲደርሱ በሩን ከፈተ ማለት ነው።

እነዚህ የመቀመጫ ሽንቁርን ሆን ብለው የተዉት የፒጃማ ማስታወቂያዎችም ዓላማቸው ሸማቾችን በቀጣይነት የፍላጎት መረጃቸውን ሰብስቦ ዒላማ ማድረግ ነው።

ቢቢሲ የምርቶቹን ባለቤቶች አይቪሮዝን እና ቺክ ሚ ኩባንያዎችን አስተያየት ለማካተት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።