ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡ ታንዛኒያ 'ክትባቱ ይቅርብኝ ባህላዊ መድሃኒት ይሻለኛል' አለች
ታንዛኒያ ለኮቪድ-19 የተሰሩ ክትባቶችን መጠቀም እንደማትፈልግና በምትኩ አገር በቀል መድሃኒቶች ላይ ትኩረት ማድረግ እንደምትፈልግ ማስታወቋ ተገለጸ።
ከኢስት አፍሪካ ጋዜጣ ጋር ቆይታ ያደረጉት የታንዛኒያ የጤና ሚኒስትር ጄራልድ ቻሚ ከውጪ የሚገቡ ክትባቶች ላይ ከድህንነትና ከውጤታማነት አንጻር ጥርጣሬ እንዳላቸው ገልጸዋል።
ሚንስትሩ ክትባቶቹ የተሰሩበት ፍጥነት እንደሚያሳስባቸውም ተናግረዋል።
ምንም እንኳን አሁን የተሰሩትና ጥቅም ላይ እየዋሉ የሚገኙት ክትባቶች ሁሉንም የደህንነትና ውጤታማነት ዓለማ አቀፍ መመዘኛዎች ቢያልፉም ሚንስትሩ ግን እምብዛም አላሳመነኝም ብለዋል።
በሌላ በኩል የታንዛንያው ፕሬዝዳንት ጆን ማጉፉሊ የኮሮረናቫይረስን በተመለከተ በሚሰጧቸው አስተያየቶችና በሚያስተላልፏቸው ውሳኔዎች የዓለምን ትኩረት መሳብ የቻሉ መሪ ናቸው።
ኮቪድ-19 ታንዛኒያ ሲደርስ ፕሬዚዳንቱ ሰዎች በቤታቸው መቆየት የለባቸውም ብለው አጥብቀው ይከራከሩ ነበር። እንዳውም ቫይረሱ እንዲጠፋ ቤተክርስቲያን እና መስጂድ ሄደው እንዲጸልዩ አበረታትተዋል።
''ኮሮናቫይረስ እርኩስ መንፈስ ነው፤ በክርስቶስ ሰውነት ውስጥ ሊቆይ አይችልም. . . . . ወዲያውኑ ይቃጠላል'' ሲሉም ተደምጠዋል ወግ አጥባቂው ክርስቲያን መሪ ጆን ማጉፉሊ።
ፕሬዝዳንቱ ከዚህ በተጨማሪ ማህበራዊ ርቀትን መጠበቅና የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ ስለማድረግ በተመለከተ ሲናገሩ ተግባራቱ ምንም ፋይዳ የላቸውም ሲሉም ተደምጠው ነበር።
ፕሬዝዳንት ጆን ማጉፉሊ ጎረቤት አገራት የእንቅስቃሴ ገደብ መጣላቸውን በመተቸትም እሳቸው ግን በዚህ መልኩ ኢኮኖሚውን መጉዳት እንደማይፈልጉ በተደጋጋሚ ገልጸዋል።
እንደውም ወርሃ ሰኔ ላይ ፕሬዝዳንት ጆን ማጉፉሊ አገራቸው ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ነጻ መሆኗን አውጀው ነበር። አነጋጋሪው ፕሬዝዳንት እንዳሉት ታንዛኒያ ከወረርሽኙ ነጻ የወጣችው በሕዝቧ ጸሎት መሆኑን ነው እንደ ምክንያት የጠቀሱት።
"እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን የኮሮናቫይረስ በሽታ ተጣራርጎ ተወግዷል" ሲሉ ዶዶማ በተባለችው ከተማ ውስጥ በአንድ ቤተክርስቲያን ተሰብስበው ለነበሩ ምዕመናን ተናግረዋል።
''በአገራችን በርካታ በቫይረስ የሚተላለፉ በሽታዎች አሉ፤ እንደ ኤችአይቪ ኤድስ ያሉትን መጥቀስ ይቻላል። ሁሌም ቢሆን ኢኮኖሚያችን መቅደም አለበት። ኢኮኖሚው እንዲተኛ መፍቀድ የለብንም፤ ሕይወትም መቀጠል አለባት'' ብለው ነበር ፕሬዝዳንቱ።
በተጨማሪም ''ሌሎች የአፍሪካ አገራት ኢኮኖሚያቸውን ቸኩለው በመዝጋታቸው ከፍተኛ ችግር ውስጥ ስለሚገቡ በቅርብ ዓመታት ምግብ ከእኛ ለመግዛት መምጣታቸው አይቀርም'' ሲሉም ተደምጠው ነበር።
ግንቦት ወር ላይ ደግሞ ታንዛኒያ ከማደጋስካር ያዘዘችውን የኮቪድ-19 'መድሃኒት' ተቀብላ ነበር።
በወቅቱ የታንዛኒያው የውጪ ጉዳይ ሚንስትር መድሃኒቱን ሲቀበሉ የሚያሳዩ ፎቶግራፎችን በኢንስታግራም ገጻቸው ላይ የለጠፉ ሲሆን በአንዱ ፎቶ ላይ የማደጋስካሩ ሚንስትር ለታንዛኒያው አቻቸው በኮቪድ-19 'መድሃኒት' የተሞላ ካርቶን ሲሰጡ ይታያል።