ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮቪድ-19፡የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት በኮሮናቫይረስ ተያዙ
የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን ፓሪስ የሚገኘው የፕሬዚዳንቱ ቢሮ አረጋግጧል።
የ42 አመቱ ፕሬዚዳንት የኮሮናቫይረስ ምልክቶች ማሳያታቸውን ተከትሎ ምርመራ ማድረጋቸውንና ለሰባት ቀናትም ራሳቸውን ለይተው እንደሚቆዩ ፅህፈት ቤታቸው ኤሊዜ ቤተ መንግሥት በመግለጫው አሳውቋል።
ፅህፈት ቤታቸው ፕሬዚዳንቱ አገሪቷን የመምራት ኃላፊነታቸውንም እንደሚቀጥሉበትና ራቅ ብለው ተግባራቸውንም እንደሚያከናውኑም አስታውቋል።
ፕሬዚዳንቱ በቫይረሱ እንዴት እንደተያዙ ቢሯቸው እንደማያውቅ ገልፆ በቅርብ የተገናኟቸውንም ሰዎች ለመለየት ክትትል እያደረገ እንደሆነም አክሎ ገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ጂን ካስቴክስም ከፕሬዚዳንቱ ጋር ቅርበት ነበራቸው በሚልም ራሳቸውን ለይተው እንደሚቆዩም ተገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአገሪቱን የኮሮናቫይረስ መከላከያ ክትባት ፖሊሲ ለምክር ቤቱ በዛሬው ዕለት እንዲያስተዋውቁ እቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም በምትኩ የጤና ሚኒስትሩ ኦሊቪየር ቬራን ይናገራሉ ተብሏል።
ሆኖም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እስካሁን ድረስ ምንም ምልክት እንዳላሳዩም ቢሯቸው ገልጿል።
የስፔኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝም ከፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ጋር በዚህ ሳምንት ሰኞ ምሳ በልተው የነበረ ሲሆን በዛሬው ዕለትም ራሳቸውን ለይተው እንደሚቆዩም ተናግረዋል ።
በዚሁ የምሳ ስብሰባ ወቅት የአውሮፓ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ቻርልስ ሚቼልና ዋና ፀሃጊ አንጄል ጉሪያ ተገኝተዋል ተብሏል። ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮም እመረመራለሁ ብለዋል።
የማክሮን ባለቤት ብሪጄት በለይቶ ማቆያም ቢሆኑም ምልክት አልታየባቸውም። ከሳቸው በተጨማሪ የፓርላማው ቃለ አቀባይ ሪቻርድ ፌራንድም በለይቶ ማቆያ ናቸው።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ በርካታ የአለም መሪዎች በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሲሆን የማክሮንን ጨምሮ ከዚህ ቀደምም ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕና የዩኬው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን መያዛቸው ይታወሳል።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሁለተኛ ዙር እያገረሸባት ያለችው ፈረንሳይ ከሰሞኑም የሰዓት እላፊ አዋጅ ጥላለች።
ወረርሽኙ ከተከሰባት እለት ጀምሮ 2 ሚሊዮን ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ 59 ሺህ 400 ዜጎቿን በኮሮናቫይረስ ማጣቷን ከጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ የተገኘው መረጃ ያስረዳል።