"የትዊተሩ ነፍሰ በላ" ሞት ተፈረደበት

በትዊተር እያማለለ የ9 ሴቶችን ነፍስ ያጠፋው ጃፓናዊ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በትዊተር እያማለለ የ9 ሴቶችን ነፍስ ያጠፋው ጃፓናዊ በመጨረሻ በሞት እንዲቀጣ ተፈረደበት፡፡

ታካሂሮ ሺራይሺ የተባለው ይህ ነፍሰ ገዳይ የፍርድ ሒደቱ በጃፓን ትልቅ ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል፡፡

የሰውየው ድርጊትም ጃፓናዊያንን አስደንግጧል፡፡

‹የትዊተሩ ነፍሰ በላ› በሚል ቅጽል በይበልጥ የሚታወቀው ይህ ሰው በ2017 ነበር ፖሊስ ሰዎችን እየቆራረጠ እንደሚገድል የደረሰበት፡፡

የሚኖርበት አፓርታማ ሲፈተሸም የገደላቸው ሰዎች ቁርጥራጭ ስጋ ተገኝቷል፡፡

ሺራዪሺ ድርጊቱን ስለመፈጸሙ ባለፈው ጥቅምት ለፍርድ ቤት ሳያቅማማ አምኗል፡፡ ‹‹የተመሰረተብኝ ክስ ሙሉ በሙሉ ትክክል ነው›› ብሎ ነበር ለፍርድ ቤቱ፡፡

ይህ የ30 ዓመት ጃፓናዊ ሴቶቹን ለመግደል በትዊተር የሚያማልለው ራሳቸውን ማጥፋት የሚሹ ሴቶችን ብቻ መርጦ ወደቤቱ በመጋበዝ ነበር፡፡

ራሳቸውን ማጥፋት የሚፈልጉ ሴቶችን አድኖ ከተዋወቃቸው በኋላ በሂደቱ አግዛችኋለሁ በማለት ቃል ይገባል፡፡ አብሯቸው ራሱን ለማጥፋትም በመስማማት ያበረታታቸው ነበር ተብሏል፡፡

ወንጀለኛው የሚኖረው በቶክዮ አቅራቢያ በምትገኝ ዛማ በምትባል ትንሽ ከተማ ውስጥ ነው፡፡

ጠበቃው የሞት ቅጣቱ እንዲቀልለት ቀደም ብለው ያቀረቡት መቃወሚያ ደንበኞቹ ራሳቸውን ለማጥፋት ቀድመው የተስማሙ መሆናቸውንና የእርሱ ድርሻ መተባበር ብቻ እንደነበር በመጥቀስ ነው፡፡

ነገር ግን ሺራይሺ የራሱን ጠበቃ መቃወሚያ በሚጣረስ መልኩ ደንበኞቹ ሳይስማሙ ጭምር ይገድላቸው እንደነበር ለፍርድ ቤት ተናግሯል፡፡

ዳኛው በመጨረሻ በሰጡት ብይን ሟቾች አንዳቸውም ነፍሳቸውን እንዲያጠፋላቸው ስምምነት አልፈጸሙም ነበር ብለዋል፡፡

ዘገባው ሺራይሺ በየትኛው መንገድ በሞት እንደሚቀጣ ያለው ነገር የለም፡፡

ፖሊስ በ2017 የወንጀለኛውን ቤት ሲፈትሽ ከ9 ሰዎች ውስጥ የሁለት ሴቶችን ጭንቅላት ተቆርጦ ማቀዝቀዣ ውስጥ ተቀምጦ አግኝቶ ነበር፡፡

የሚገድላቸውን ሴቶች ሰውነት ከበለተው በኋላ በመልክ በመልኩ በሳጥን ውስጥ ያስቀምጣቸው እንደነበር የመርማሪ ፖሊስ የምርመራ ውጤት ያሳያል፡፡

በየጊዜው ደብዛቸው የሚጠፉ ሴቶችን ፍለጋ ላይ የነበረ ፖሊስ የወንጀለኛው መኖርያ ቤት አካባቢ የሬሳ ሽታ መኖሩን ከጎረቤት ጥቆማ ማግኘቱን ተከትሎ ነው ያን ጊዜ የ27 ዓመት ወጣት የነበረውን ሰው ጠርጥሮ ምርመራ የጀመረበት፡፡