ሎተሪ በአንድ ጀንበር ሚሊዬነር ያደረጋቸው ሰዎች ምን አሉ?

ይበለውና ዛሬ ድንገት ዝሆን ሎተሪ ቢደርስዎ ምን ያደርጉበታል? የሀብታሞች አገሮቹ ዝሆን ሎቶሪ።

ምናልባት እንደ ዝሆን ጎምለል እያሉ ዓለምን ይዞሩ ይሆናል። ምናልባት ቀሪ ሕይወትዎን በተድላ ይመሩ ይሆናል።

ምናልባት ከዚያ በኋላ በደስታ ሕንድ ውቅያኖስ ጠልቀው በሐሴት ከአትላንቲክ ውቅያኖስ ብቅ የሚሉ ይመስልዎት ይሆናል።

ነገሩ እንደዚያ ላይሆን ይችላል ብለው አስበው ያውቃሉ?

በዚህ ጉዳይ ላይ አንድ መናጢ ጋዜጠኛ ከሚዘባርቅ የደረሳቸው ቢናገሩት ሳይሻል አይቀርም።

አዲ ጉድቻይልድ ባለፈው ዓመት የ71 ሚሊዮን ፓውንድ ሎተሪ አሸነፈ።

ዩሮ ሚሊዮንስ የሚባለውን ዝሆን ሎቶሪ ነበር ያሸነፈው።

ከዚህ በኋላ ጡረታ ወጥቼ ቁጭ ብዬ እበላለሁ ብሎ ነበር።

ቁጭ ብሎ መብላት ደስታን የሚያመጣ ነገር እንዳልሆነ የተረዳው ግን ዘግይቶ ነው። አዲ ብቻውን አይደለም። ጄን አለች።

"ሪ ማሸነፌ ሕይወቴን አተራማምሶታል"

ጄን ሬስቶሪክ ሎተሪ ሳይደርሳት በፊት ጄን ፓርክ ነበር ስሟ።

ስሟን እንድትቀይር ብቻም ሳይሆን ሕይወቷም እንዲቀየር ያደረጋትን ሎተሪ ያሸነፈችው የዛሬ 4 ዓመት ግድም ነበር።

በብሪታኒያ ታሪክ ሎተሪን በማሸነፍ ልጅ አግሯ እሷ ናት፤ ጄን።

ሎተሪው ሲደርሳት የሆነ አስተዳደር ቢሮ ውስጥ ትንሽዬ ሥራ ነበረቻት። በኤደንብራ በትንሽዬ አፓርታማ ውስጥ ከእናቷ ጋር ትኖር ነበር።

ጄን አንድ ሚሊዮን ዶላር ሎተሪው እንደደረሳት በፌስቡክ አወጀች። ከዜናው ጋር የመደነቅ ኢሞጂ የሚሉትን (እኛ ለዚህ የሎቶሪ አዝናኝ ታሪክ ደቂቀ ገጽታ ብለን የምንጠራውን የማኅበራዊ ሚዲያ አሻንጉሊት ሳቅ) አስከተለች።

መጀመሪያ ያደረገችው ውድ የቺኋሄ ቡችላ ዝርያን (Chihuahua dog) የሳሎን ውሻ መግዛት ነበር። ፕሪንሰስ ብላ ጠራቻት።

ከዚያ ውድ የንግድ ስም ያለውን አንድ ቦርሳ መግዛት ህልሟ ነበር። እንዳሰበችውም የሉዊ ቪቶ (Louis Vuitton) ቅንጡ ፋሽን የእጅ ቦርሳ ገዛች።

በእነዚህ ሁለት ወጪዎች ብቻ 10 ሺህ ፓውንዶች እልም ብለው ሄዱ።

ከዚያ በኋላ ግን ግራ ገባት።

ሕይወቴ እላዬ ላይ ሲፈርስ ነበር የሚታየኝ ብላለች ከሦሰት ዓመት በፊት በሰጠችው አንድ ቃለ ምልልስ።

በየቀኑ ስነሳ የማስበው ከገንዘብ ጋር የተያያዘ ነገር ነበር። ያ ስሜት ደስ አይልም ትላለች። ይህን ሐሳቧን ከአእምሮዋ ማውጣት ግን አልቻለችም። "ምነው ይሄ ሎተሪ ጭራሽ ባልደረሰኝ" ብላ እስከመመኘት ደርሳም ነበር።

የአንድ ሚሊዮን ፓውንድ ሎተሪ ለ17 ዓመት ልጅ አደገኛ ነገር ነው። ይሄ ምንም አጠራጣሪ አይደለም።

"ምን ማድረግ ነው ትክክል የሚለውን ነገር የሚመራኝ ሰው አልነበረም" ትላለች።

ሎተሪው ከደረሳት በኋላ ወዳጅ ዘመዶቿ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ዓይን ዓይኗን ማየት ጀመሩ። ይቺ ልጅ "የገንዘብ ችግራችንን የምትቀርፍልን" በሚል መነጽር ብቻ ያይዋት ጀመረ።

"ሰዎች እኔን የሚፈልጉኝ ከሎተሪ ገንዘቡ ጋር በተያያዘ ብቻ መሆኑን ስረዳ ጭንቀት ውስጥ ገባሁ" ትላለች።

የሎተሪው ድርጅት ኃላፊ ካሜሎት በበኩላቸው "ለልጅቷ የሥነ ልቦና ደጋፍ ብቻም ሳይሆን ገንዘቧን እንዴት ማስተዳደር እንዳለባት የሚያማክራት ሰው በነጻ አቅርበንላት ነበር" ሲሉ ጥፋቱ ከእነሱ እንዳልሆነ ያስረዳሉ።

"ሚሊየነር ብሆንም ሥራዬን እወደዋለሁ"

ሱ ሪቻርድስ በ2016 ወደ ቤት እየሄደች ነበር። እግረ መንገዷን ሱፐር ማርኬት ገብታ ፈጣን ሎተሪ ገዛች። ነገሩን ከቁብም አልቆጠረችውም ነበር።

እንደጨዋታ ነበር የገዛችው።

ቤት ገብታ ፋቀችው። 3 ሚሊዮን ፓውንድ አሸናፊ አደረጋት።

ደስታዋ ወደር አልነበረምው። ከባሏ ጋር ወደ ኢሴክስ ከተማ ሄደው ቤት ገዙ። አራት መኪኖችን እላዩ ላይ መረቁበት። ከዚያ በኋላ ደግሞ ዓለምን ዞር ዞር ብለው ማየት ጀመሩ።

ለልጆቻቸውም የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ አሟሉ። ባለፈው ዓመት ሚስ ሪቻርድ ከባለቤቷ ጋር ሆና ሎተሪ ያሸነፉበትን አራተኛ ዓመት አከበሩ።

የቤታቸው ግቢ አፀድ ውስጥ በርከት ያለ ብር አውጥተው በሻምፓኝ ነበር ያከበሩት።

ሚስ ሪቻርድስ ሚሊየነር ብትሆንም ቅሉ በሳምንት 90 ሰዓት አዛውንት ተንከባካቢ ሆና ትሰራለች።

ምን በወጣሽ ትለፊያለሽ? ስትባል "ሥራዬን እወደዋለሁ" ነው መልሷ።

ምናልባት ከሚሊዮን ዶላሩ ባሻገር የደስታዋ ምንጭ ሥራዋ ሳይሆን አልቀረም።

"ሚሊየነር መሆ ያን ያህልም አልደነቀኝም"

በታኅሣስ 2017 ሜሊሳ ኤድ ወደ ሐል ነዳጅ ማደያ ገባች። እሷም እንዲሁ የሚፋቅ ሎተሪ ገዛች። ፈጣኑን።

በሦስተኛው ቀን ባንክ ደብተሯ አብጦ ሊፈነዳ ደርሶ አገኘችው። 5 ሚሊዮን ፓውንድ ገብቶበታል።

"በአንድ ጀንበር የባንክ ደበተሬ ከአንደ ፓውንድ ወደ 5 ሚሊዮን ፓውንድ ተመነደገ" ብላ ነበር ለቢቢሲ።

ሜሊሳ ሚሊየነር ከመሆኗ በፊት ማታ ማታ የታክሲ ሾፌር ነበረች። ቤሳ ቤስቲን አልነበራትም።

"ሕይወት በጣም ፈተና ሆናብኝ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ገንዘብ ስለማይኖረኝ እራት እንኳን የማልበላበት ጊዜ ነበር" ትለላች።

ካሸነፈች በኋላ 3 ሚሊዮን ፓውንዱን ኢንቨስት አደረገችው። ቤት ገዛች። የቤተሰቧንና የጓደኞቿን እዳቸውን ከፋፈለች። ሕይወታቸውን ለወጠች።

ይህን ሁሉ አሳክታም እንዲህ ትላለች።

"ሰዎች ሎተሪ ሁሉን ነገር የሚቀይር ይመስላቸዋል። ያን ያህልም የሚያስደንቅ ነገር አይደለም። ከጊዜ በኋላ ሁሉም ነገር ወደነበረበት ይመለሳል" ትላለች።

"ብዙ ሰዎቸ ገንዘብ ሁሉንም ችግር የሚቀርፍ ይመስላቸዋል። ውሸት ነው። ሚሊየነር መሆን ደስተኛ መሆን ማለት እንዳልሆነ እኔ ህያው ምስክር ነኝ" ብላ ነበር ለቢቢሲ።

"በኬክ ላይ የተንሸራተትኩ ያህል ተሰማኝ"

ሪቻርድና ካቲ ብራውን ጋዜጠኞች ነበሩ።

ሳያስቡት 6 ሚሊዮን ፓውንድ አሸነፉ። ለነገሩ ሎተሪ ማን አስቦት አሸንፎ ያውቃል።

እነ ሪቻርድ ወዲያውኑ ዓለምን መዞር ጀመሩ።

በበረዶ ወደተሸፈነው የአንታርክታካ አህጉር ሄደው በረዶ ሸርተቴ ተጫውተዋል። ህልማቸውም እሱ ነበር። "በኬክ ላይ የመንሸራተት ያህል ነው" ይላሉ የሕይወታቸውን መቃናት ሲያሰምሩበት።

ባልና ሚስቱ አሁን ጡረታ ወጥተዋል። በሰሜን ዋልታ በባህር ቀዘፋ እየተጫወቱ ዓመቱን ሙሉ ሽር ብትን እያሉ ለማሳለፍ ነው ያቀዱት።

"በሎተሪ ያገኘነው ገንዘብ በሕይወታችን ከሚያስፈልገን የገንዘብ መጠን እጅግ የበዛ ነው። ስለዚህ በተቻለ መጠን ቤተሰባችን ከእኛ መልካም ዕድል ተጋሪ ማድረግ ነው የምንሻው" ብለዋል ለቢቢሲ።

ሚሊየነር መሆን የገንዘብ ችግርን ይቀርፍ ይሆናል እንጂ በራሱ የደስታ ምንጭ እንዳልሆነ ግን ያሰምሩበታል። ባልና ሚስቱ።