ቻርልስ ዳርዊን ፡ ከጠፋ 20 ዓመት የሆነውና እጅግ ውዱ የዳርዊን ማስታወሻ ደብተር እየተፈለገ ነው

ዝነኛው ኬምብሪጅ ዩኒቨርስት ቤተ መጻሕፍት የሥነ ፍጥረት ሊቁን የቻርለስ ዳርዊንን ማስታወሻ ደብተር የሰረቁ እንዲመልሱለት የልመና ማስታወቂያ አውጥቷል።

ማስታወሻ ደብተሩ ከኬምብሪጅ ቤተ መጻሕፍት 'ከተሰረቀ' 20 ዓመታትን አስቆጥሯል።

በዚህ ማስታወሻ ደብተሩ ላይ ይገኙ ከነበሩ ብርቅዬ ጽሑፎች አንዱ ዳርዊን በዝግመተ ለውጥ የሥነ ሕይወት ዝርያዎች ሰንሰለትን ያመላከተበት "የሕይወት ዛፍ" ንድፍ (Tree of Life sketch) ይገኝበታል።

ለ20 ዓመታት እነዚህ ማስታወሻዎች የት እንደሚገኙ የቅርስ ጥበቃ ባለሙያዎች ፍለጋ አካሄደዋል።

ሆኖም የማስታወሻውን ዱካ ማግኘት አልቻሉም። በመጨረሻም አሁን የዳርዊን ማስታወሻ ተሰርቆ ሊሆን እንደሚችል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል።

ለዚህም ነው አሁን ማስታወሻዎቹ ያሉበትን የሚያውቅ፣ ፍንጭ የሚሰጥ ማንኛውም መረጃ አለኝ የሚል ዜጋ ኬምብሪጅ ቤተ መጻሕፍን በመምጣት ወይም በስልክና ኢሜይል ጥቆማ እንዲሰጥ የተለመነው።

ማስታወሻውን የሰረቀው ሰው ማንነቱን እንደደበቀ ለኬምብሪጅ ሊያቀብልም ይችላል ተብሎ ተበረታቷል።

የኬምብሪጅ ዩኒቨርስቲ የቤተ መጻሕፍቱ ተጠሪ ዶ/ር ጄሲካ ጋርድነር "ይህ ልብ የሚሰብር ክስተት ነው። ሆኖም ማስታወሻዎቹን ለማግኘት የማንፈነቅለው ድንጋይ አይኖርም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

እነዚህ የዳርዊን ማስታወሻዎች ለመጨረሻ ጊዜ የታዩት የዛሬ 20 ዓመት ግድም በወርሃ ኅዳር ላይ ነበር።

ከማኑስክሪፕት ክፍል ወጥተው ፎቶግራፍ እንዲነሱ የሚጠይቅ የውስጥ ማስታወሻ ልውውጥ ከተደረገ ከሁለት ወራት በኋላ ነው የገቡበት የጠፋው።

ከዚህ በኋላ የማስታወሻዎቹ ገጾች ወደ ጊዜያዊ ስቱዲዮ ተወስደው ነበር። ምክንያቱም የዩኒቨርስቲው ቤተ መጻሕፍት ዋና ሕንጻ እድሳት ላይ ስለነበረ ነው።

ከሁለት ወራት በኋላ ግን ድንገት ፍተሻ ሲደረግ እጅግ ብርቅዬ የሆኑት የዳርዊን ማስታወሻዎች ከቦታቸው አልነበሩም።

"በኅዳር ወር 2000 ዓ.ም ፎቶግራፍ አንስተናቸው ነበር። ከዚያ በኋላ በነበሩት ወራት ግን ምን እንደተከሰተ የሚያውቅ የለም" ይላሉ ዶ/ር ጋርድነር።

የዳርዊን ብርቅዬ ማስታወሻዎች በጠፉ ሰሞን የቤተ መጻሕፍቱ መኮንኖች ምናልባት የተሳሳተ ቦታ ተቀምጠው ነው በሚል ተዘናግተው ነበር።

ይህም በመሆኑ ነው ለእነዚህ ሁሉ ዓመታት በኬምብሪጅ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ጥልቅ ፍተሻ ሲደረግ የነበረው።

ብዙ ሰዎች እንዴት አንድ ማስታወሻን በአንድ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ የተቀመጠበትን ቦታ ለማግኘት ለዓመታት ፍለጋ ይደረጋል ይሉ ይሆናል።

በኬምብሪጅ ዩኒቨርስቲ በሚገኘው ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ያሉት መጻሕፍትና ሰነዶች ቁጥራቸው እጅግ በጣም ብዙ በመሆኑ በቤተ መጻሕፍቱ ያሉት መደርደሪያዎች ቢቀጣጠሉ ከ200 ኪሎ ሜትር በላይ እንደሚሸፍኑ ይነገራል።

ይህ ብቻም አይደለም፤ በቤተ መጻሕፍቱ 10 ሚሊዮን ካርታዎችና ረቂቅ ጽሑፎች (ማኑስክሪፕትስ) ይገኛሉ። ከእነዚህ 10 ሚሊዮን ረቂቆች ውስጥ ፈልፍሎ የዳርዊንን ማስታወሻ ማግኘት አማዞን ጫካ ውስጥ የወደቀች ሳንቲም እንደመፈለግ ሆኗል።

የቻርለስ ዳርዊን ማስታወሻን ለማግኘት ለዓመታት ፍለጋው የቀጠለውም ከእነዚህ የረቂቅ ጽሑፎች ጫካ ውስጥ በአንዱ ተሰንጎ ሊሆን ይችላል የሚል የተስፋ ጭላንጭል ስለነበረ ነው።

በዚህ ዓመት አንድ የመጨረሻ እልህ አስጨራሽ ፍለጋ ይደረግ በሚል ዶ/ር ጋርድነር ባለሙያዎችን በየሼልፉ አሰማርተው ነበር። እያንዳንዱ ባለሙያ የተመደበበትን ሼልፍ ብቻ እንዲፈትሽም ተደርጎ ነበር።

የቻርለስ ዳርዊንን ደብዳቤዎችና ሥዕሎች እንዲሁም ሌሎች መጻሕፍቱን የያዙ 189 ሳጥኖችን ጨምሮ ሰፊ ብርበራ የተደረገ ሲሆን ይህ ታሪካዊ የዳርዊን ማስታወሻ ግን ሊገኝ አልቻለም።

ላለፉት 20 ዓመታት የሆነ ቦታ ተወሽቆ ይሆናል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበት የነበረው ፍለጋ በመጨረሻ ተስፋ አስቆራጭ ሆኖ ለአዲስ ድምዳሜ በቅቷል።

"አሁን የዳርዊን ማስታወሻ ተሰርቋል የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰናል" ይላሉ የቤተ መጻሕፍቱ ኃላፊ የሆኑት ሴት ዶ/ር ጋርድነር።

ኬምብሪጅ ዩኒቨስቲ የዚህን የመጨረሻ ድምዳሜ ተከትሎ ለፖሊስ ጉዳዩን አሳልፎ የሰጠ ሲሆን ፖሊስ በበኩሉ ለብሔራዊ የጠፉ ቅርሶች መዛግብት ቢሮ ጉዳዩን አሳውቋል።

ፖሊስ የዳርዊን ማስታወሻ በኢንተርፖል የጠፉ ውድ ቅርሶች መመዝገቢያ ቋት ውስጥ እንዲካተትም አድርጓል።

በ1837 ቻርለስ ዳርዊን የ28 ዓመት ወጣት ነበር። ለንደን ይገኝ በነበረው ቤቱ ቀይ ሽፋን በነበረው ማስታወሻ ደብተሩ ጫፍ ላይ አንድ ነገር ጻፈ። የጻፈው ቃል "ሳስበው!" ወይም "I think" የሚል ነበር። ከዚያም እንደነገሩ የዛፍ ቅርንጫፎች ንድፍ ሰራ።

ያን ጊዜ ገና ከጋላፓጎስ ደሴት መመለሱ ነበር። ከዚህ ጉዞው በኋላ ከፍተኛ መነቃቃት ውስጥ ነበር። የሰው ልጅን አመጣጥና የዝግመተ ለውጥ ቅብብሎሽን ለመረዳት ይጨነቅም ነበር።

ከዚች እንደ ዋዛ ከተሳለች የዛፍ ንድፍ በኋላ ዳርዊን ዓለምን ያነቃነቀ ጽንሰ ሐሳብ አበረከተ።

ከዚያች ዕለት የጀመረ ለ20 ዓመታት ጥልቅ ምርምር በማድረግ በኅዳር 1859 ዳርዊን "ዘ ኦሪጅንስ ኦፍ ስፒሺየስ"ን አሳተመ። በዚያ መጽሐፉ ያቺ 'የሕይወት ዛፍ ንድፍ' ተካታበት ነበር።

የዳርዊን ማስታወሻ ባልተፈተሹ የኬምብሪጅ ቤተ መጻሕፍቱ ክፍሎች ውስጥ አንድ ዙር ለማሰስ ተጨማሪ 5 ዓመታትን ይፈልጋል።

ሆኖም ግን ኬምብሪጅ ዩኒቨርስቲ የዳርዊን ማስታወሻ ተሰርቋል ብሎ ማመንን መርጧል።

ኃላፊዋ "እኛም ፍለጋችንን እናጧጠፋለን፣ ፖሊስም ሥራውን ይሥራ፣ ኅብረተሰቡም ጥቆማ ይስጠን" ይላሉ።

ዶ/ር ጋርድነር የቻርለስ ዳርዊን ማስታወሻ የት ሊሆን ይችላል ለሚለው ጥያቄ መላምት ማስቀመጥ አይፈልጉም። ሆኖም የሰረቀው ሰውም ቢሆን ቢያቀብላቸው አይጠሉም።

"ምናልባት የሆነ ሰው አልጋ ስር ወሽቆት ሊሆን ይችላል። መሸጥ ፈልጎ አልቻለ ይሆናል። ይህ መልካም አጋጣሚ ነው። ማስታወሻውን የሰረቀው ሰው ማንነቱን ሳይገልጽ አስቀምጦልን ቢሄድ እንዴት ጥሩ ነበር?" ይላሉ ዶ/ር ጋርድነር።