"ጌም፣ ስልክና ቲቪ የልጆችን የአእምሮ ዕድገት እያቀጨጩ ነው"-ተመራማሪዎች

Siblings playing on their phones

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኮምፒዩተር እና ሞባይል ስልክ ላይ የሚጫኑ ጌምዎች እና ቴሌቪዥን የልጆችን የአእምሮ ዕድገት እያቀጨጩ ነው ሲሉ ተመራማሪዎች አስጠነቀቁ።

"በልጆቻችን ላይ እየፈጸምነው ያለው ግፍ ይቅር የማይባል ነው" ይላሉ ሚሸል ደስመርጌት። እኚህ ሰው ፈረንሳዊ ሳይንቲስት ናቸው። ከሰሞኑ ዓለምን እያነጋገሩ ነው።

በተለይም በትውልዶች የአእምሮ ምጥቀት ዙርያ በጻፉት መጽሐፍ ነው እያነጋገሩ ያሉት።

"በዚህ ዘመን የሚወለዱ ልጆችን ድንዙዝ እያደረግናቸው ነው፤ ይህም የሚሆነው ብዙ ጌሞችን፣ ብዙ የስክሪን ሰዓቶችን ስለፈቀድልናቸው ነው፤ ሳናውቀው ስንፍናን እያወረስናቸው ነው" ይላሉ።

ፕሮፌሰር ሚሸል የኒውሮሳይንስ ሊቅ ናቸው። ዘለግ ላሉ ዓመታት በጉዳዩ ዙርያ ጥናት አድርገው የደረሱበት ሐቅ አንድ ነው። ይህም በዲጂታል ዘመን የተወለዱ ልጆች የአእምሮ ምጥቀት ልኬታቸው (IQ) በሚያስደነግጥ ሁኔታ እያሽቆለቆለ መሆኑን።

ብዙ ወላጆች በተቃራኒው ያስባሉ። ለልጆቻቸው ጌምና ስልክ በገፍ ያቀርቡላቸዋል።

ልጆቻቸው ስልክ ነካክተው በራሳቸው መክፈታቸው የአእምሮ እድገት ልቀት መስሎ ይታያቸዋል።

"ልጄን እኮ…" ብለው ማዳነቅ የሚወዱ ወላጆች ብዙ ናቸው።

ልጆቻቸው ፊልም ተመልከተው መሳቃቸው በራሱ የብልህነታቸው ማሳያ ያደርጉታል።

በመላው ዓለም ልጆች ረዥም ሰዓት በዲጂታል ዓለም ውስጥ ቀልባቸው ይሰወራል። ይህ እንዲሆን የፈቀደው ትውልድ በልጆቹ ላይ ይቅር የማይባል ግፍ ነው እየፈጸመ ያለው ይላሉ ፕሮፌሰር ሚሸል።

የዲጂታል ቁሶች (ስልክ፣ ጌም፣ ቴሌቪዥንና የመሳሰሉት) የልጆችን የአእምሮ ዕድገት እያቀጨጩ ነው ባይ ናቸው ፕሮፌሰሩ።

እኚህ ጎምቱ ሳይንቲስት ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት ልጆችን ዲጂታል በማድረግ ሳናውቀው "መጪ ዘመናቸውን እያጨለምነው ነው" ብለዋል።

አሁን የእሳቸው ሐሳብ በሳይንስ ማኅበረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ክርክር ቀስቅሷል።

በቅርብ ለንባብ ባበቁትና ከፍተኛ ሽያጭ ባስመዘገበው መጽሐፋቸው በዲጂታል ቁስና በልጆች ዙርያ የነበረውን ሙግት ሌላ ደረጃ አድርሰውታል።

የመጽሐፋቸው ርዕስ በራሱ የፕሮፌሰሩን ቁጣ ያዘለ ነው። "The Digital Cretin (or Idiot) Factory" ይላል።

"ዲጂታሉ ዓለም፡ የድድብና ፋብሪካ" ብለን ወደ አማርኛ ልንመልሰው እንችላለን።

ርዕሱ ለገበያ የተቃኘ ቢመስልም ሳይንቲስቱ ሙግታቸውን በደረቅ የሳይንስ ሐቆች አስደግፈው፣ ሳይንሳዊ ቅቡልነቱን ጨምረው ነው ያቀረቡት።

ፕሮፌሰሩ በፈረንሳይ የጤና ምርምራና ጥናት ማዕከል ዳይሬክተር ናቸው። በዓለም ላይ ስመ ጥር በሆኑ ዩኒቨርስቲዎች አስተምረዋል። ለምሳሌ ኤምአይቲ ነበሩ፣ ካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲም አስተምረዋል።

አሁን እሳቸው የጻፉት መጽሐፍ ልጆችን እንዴት ማሳደግ አለብን በሚለው ጉዳይ ላይ ዓለም አቀፍ ትኩስ ክርክር የፈጠረውም ሳይንቲስቱ ካላቸው ገናና ቦታ የተነሳ ነው። ቸል የሚባሉ ሰው አይደሉም።

የጻፉት መጽሐፍ በፈረንሳይ ቁጥር አንድ ተነባቢ ከመሆኑም ባሻገር ወደ ጣሊያንኛ፣ ስፓኒሽና ሌሎች ቋንቋዎች ተመልሶ በስፋት እየተነበበ ነው።

Toddler playing with a mobile phone

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

መጽሐፉ ምን ይላል?

የመጽሐፉ ዋንኛ ማጠንጠኛ ኢንተርኔት ከተፈጠረ በኋላ የመጣው ትውልድ ከወላጆቹ ያነሰ ምጥቀተ አእምሮ (IQ) አለው የሚል ነው።

የአእምሮ ምጥቀት ምዘናዎች፣ እንቆቅልሾችን መጨረስ፣ ነገሮችን አዙሮ ማየት፣ ተግባራትን በፍጥነት መከወን መለኪያዎች ናቸው። አንድ ሰው እነዚህን እንቆቅልሾችም ሆኑ ተግባራት ለማከናወን የሚፈጅበት ጊዜ አልያም አለመቻሉ ተመዝኖ ነጥብ ይሰጣል።

ነገሩ በተወሰነ መጠን የአንድን ግለሰብ ብልህነት መለኪያ ነው ማለት ይቻላል።

እኚህ ሳይንቲስት ባደረጉት ጥናት ዓለም በኢንተርኔት መጥለቅለቅ ከጀመረች ጀምሮ አዲሱ ትውልድ የብልህነት ደረጃቸው አሽቆልቁሏል። ከአባት ከእናቱ ያነሰ የአእምሮ ምጥቀት ልኬት ነው እያስመዘገበ ያለው።

ከዚህም ባሻገር ጥናቶች በተደጋጋሚ ያረጋገጡት ነገር ቢኖር በሁሉም የሰው ልጅ ታሪክ ትውልድ የሚፈጥራቸው ልጆች ከራሱ እየተሻሉ ነበር የመጡት። ኢንተርኔት ከተፈጠረ በኋላ ግን ይህ ሐቅ እንቅፋት ገጥሞታል።

በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ትውልድ ከቀደምት ትውልድ ያነሰ የአእምሮ ምጥቀት እያስመዘገበ ነው።

ቢቢሲ ለኚህ ሳይንቲስት አንድ ጥያቄ አንስቶላቸው ነበር። በእርግጥ ይህ ትውልድ ከወላጆቹ ያነሰ አነስተኛ ንቃትና ብልሀት በማሳየት የመጀሪያው ትወልድ ነው?

የሳይንቲስቱ ሚሸል ምላሽ ፈጣን ነው። "አዎ!" የሚል ነበር።

አንድ ትውልድ ወደሚቀጥለው ትውልድ ሲሸጋገር የሚኖረው የአእምሮ ብርታትና መሻሻል "ፍሊን ኢፌክት" ('Flynn effect') ተብሎ ይጠራል።

ይህ ስም የተሰጠው ይህን ሐቅ ለመጀመርያ ጊዜ ከደረሰበት ሳይንቲስት ስም በመነሳት ነው። ግኝቱም በእሱ ስም ይጠራል።

የጽንሰ ሐሳቡ ፍሬ ነገር አዲስ ትውልድ ምንጊዜም ካለፈው ትውልድ የተሻለ ጭንቅላት ይኖረዋል የሚል ነው። በአመዛኙ ይህ ሐቅ በሳይንሱ ማኅበረሰብ ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ ነው።

የሚደንቀው ታዲያ በብዙ አገራት በተደረጉ ሰፋፊ ጥናቶች ይህ 'ፍሊን ኢፌክት' ለአዲሱ ትውልድ አልሰራም። ያልሰራው ደግሞ ኢንተርኔት የዓለም ልዩ ክስተት ሆኖ አእምሮንና ጊዜን መቆጣጠር ከጀመረ በኋላ ነው።

ይህ የትውልድ ልቀት ሰንሰለት የተበጠሰው ለኢንተርኔት በተንበረከከው ትውልድ ነው።

እርግጥ ነው የምጡቅ አእምሮ ልኬት (IQ) በብዙ ሁኔታዎች ተጽእኖ ሥር ሊወድቅ ይችላል። የጤና ሁኔታ፣ የትምህርት ፖሊሲና አተገባበር፣ የተመጣጠነ ምግብ ማግኘት አለማግኘት ወዘተ የጠቀሳሉ።

ሆኖም ተቀራራቢ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ባለባቸው አገራት በተደረገ ጥናት የአእምሮ ምጥቀት ልኬት (IQ) ለመጀመርያ ጊዜ በአዲሱ ትውልድ ማሽቆልቆል አሳይቷል።

ልጆች ከወላጆቻቸው በእጅጉ ያነሰ የብልህነትና የምጡቅነት ውጤት አሳይተዋል። ይህ ሐቅ ቢያንስ በብልጹጎቹ ኖርዌይ፣ ዴንማርክ፣ ፊንላንድ፣ ኔዘርላንድና ፈረንሳይ ታይቷል።

ሌላው አንኳር ጥያቄ የአእምሮ ምጡቅነት ልኬት መውረድን ያመጣው የኢንተርኔት መምጣት ነው ብለን እርግጠኛ ለመሆን የሚያበቃን ምንድነው? የሚለው ነው።

እርግጥ ነው መቶ በመቶ ኢንተርኔት ነው ትውልዱን ያደናቀፈው ብሎ መናገር ይከብዳል። ለምሳሌ ማዳበርያ ያበለጸገው ምግም መመገብ፣ ወይም ለተበከለ አየር መጋለጥ ወዘተ ሌሎች ምክንያቶች ሊባሉ ይችሉ ይሆናል።

ሆኖም በፕሮፌሰር ሚሸል ጥናት የተደረሰበት አንድ ሐቅ ልጆች ስክሪን ላይ ረዥም ጊዜያቸውን ማጥፋታቸው ለድንዛዜ እያበቃቸው መሆኑ ነው።

ተደጋጋሚና ሰፊ ጥናቶች መልሰው መላልሰው ያረጋገጡት ሐቅ ቢኖር ቴሌቪዥን፣ ኢንተርኔት፣ ስልክና ጌም ላይ መጣድ የአእምሮ ምጡቅነትን ይቀንሳል።

ይህም የሚሆነው የብልህነታችን መገለጫ የሆኑት ቋንቋ፣ ትኩረት ማድረግ፣ ነገሮችን ማስተዋል እና ባሕል በስክሪኖች ምክንያት ይሸረሸራሉ።

እንዴት ነው ስክሪን አእምሮ ብቃትን የሚያዳክመው?

ምክንያቶቹ ተለይተዋል። አንዱ ከሰዎች ጋር የሚኖረን የተግባቦት ጊዜ መውረድ ነው። ሌላው ትኩረት መስጠት የምንችልበት ጊዜ በእጅጉ ማነሱ ነው። የትኩረት ርዝማኔ ለሰከንዶች አልያም ለአጭር ደቂቃዎች ብቻ የሚዘልቅ ሆኗል።

ብዙ የዚህ ትውልድ አባላት አንድን ነገር ዘለግ ላለ ሰዓት በጥሞና መስማት ወይም ማስተዋል አይችሉም። ልባቸው ይባትታል። የቋንቋ እድገትና የስሜት እድገታችን በስክሪን ድጋፍ የቆመ ይሆናል።

ስክሪን ይህን ትውልድ ብዙ ስሜቶቹን ሸርሽሮበታል። የማዘን፣ የማጤን፣ የመደሰት ስሜቶች አርቴፊሻል ሆነዋል።

የመጽሐፍ ንባብ አእምሮ እንዲያሰላስል ያግዛል። የሥዕል ጥበብ፣ ሙዚቃና ሌሎችም እውናዊ ጥበቦች የአእምሮን ሙሉ ትኩረት ይወስዳሉ። የአእምሮ ጤናማ ዕድገትን ያሳልጣሉ። ስክሪኖች ግን ከዚህ በተቃራኒው ናቸው። ግልብነት፣ የእውነተኛ ስሜት ማጣት፣ ስለምንም ግድ አለመስጠት የስክሪን አመሎች በዚህ ትውልድ ላይ ያመጡበት ጣጣ ነው።

በአጠቃላይ ጌሞች፣ ስልኮች፣ ቲቪና ኢንተርኔት አእምሮ አቅሙን እንዳያውቅ እያታለሉ እድገቱ እንዲገታ የሚያደርጉ ሆነው ተገኝተዋል።

የአእምሮ መለጠጥ ለእድገቱ እጅግ አስፈላጊ ነው። ስክሪን አእምሮ እንዳይለጠጥ ያደርገዋል። ይህን እድገቱን ያቀጭጫል።

በሌላ ቀላል ምሳሌ ነገሩን ማስቀመጥ ይቻላል።

ጡንቻ በስፖርታዊ እንቅስቃሴ ይጎለብታል። ስክሪን የሚያይ ሰው ግን አንድን የስፖርት ውድድር ሶፋ ላይ ቁጭ ብሎ ፈንዲሻ እየቃመ ብቻ በተደጋጋሚ በመመልከት ጡንቻው እንዲጎለብት የመሻት ያህል ነው።

ፕሮፌሰር ሚሸል በመጽሐፋቸው ወላጆችን "ድድብና አታውርሱ" የሚሉት ለዚሁ ነው።