ኮሮናቫይረስ፡ የአውሮፓ ሕብረት 300 ሚሊዮን የክትባት ብልቃጦችን ለመግዛት ተስማማ

የፎቶው ባለመብት, BioNTech SE 2020
የአውሮፓ ሕብረት 90 በመቶ ውጤታማ ነው የተባለለትን 300 ሚሊየን የኮቪድ-19 ክትባት ብልቃጦችን ለመግዛት ከባዮኤንቴክ እና ፋይዘር ጋር ከስምምነት ደረሰ።
የመድሀኒት አምራቾች ድርጅቶች እንዳስታወቁት በያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት መጨረሻ ላይ ለአውሮፓ ሕብረት ክትባቱን ማስረከብ ይጀመራል።
ነገር ግን የአውሮፓ ሕብረት ክትባቱ መቼ ይከፋፈላል በሚለው ላይ ምንም አይነት መረጃ ከመስጠት የተቆጠበ ሲሆን ይህን ከማድረጋችን በፊት ቀደም ብለው መጠናቀቅ ያለባቸው በርካታ ስራዎች አሉ ብሏል።
በሁለቱ ኩባንያዎች ይፋ የተደረገው አዲሱ የኮሮናቫይረስ ክትባት 90 በመቶ ሰዎችን በኮቪድ-19 ከመያዝ ታድጓል የተባለ ሲሆን ግኝቱ ለሳይንስና ለሰው ልጅ ትልቅ እድልም ነው ተብሏል።
ፋይዘርና ባዮኤንቴክ ክትባቱን ከሶስት ሳምንታት በኋላ ጥቅም ላይ ለማዋል ጥያቄ ማቅረባቸውን ገልጸዋል።
በቁጥር የበዙ ክትባቶች የመጨረሻ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ የተነገረ ሲሆን ይህ ክትባት ተስፋ ከተጣለባቸው ውስጥ ቀዳሚው ነው ተብሏል።
ከዚህ ቀደም የተደረገው ሙከራ ክትባቱ ሰውነታችን ከበሽታው ጋር እንዲለማመድና አንቲቦዲዎችን እንዲያዳብር መርዳቱ የተስተዋለ ሲሆን ሌላው ደግሞ ቲ-ሴል በመባል የሚታወቀው የመከላከል አቅምን የኮሮናቫይረስን መዋጋት እንዲችል አድርጎታል ተብሏል።
ለሙከራው በሁለት ዙር በሶስት ሳምንት ልዩነት ክትባቱ መሰጠቱ ታውቋል።
የአውሮፓ ሕብረት የጤና ኮሚሽነሯ ስቴላ ኪሪያኪድስ ሕብረቱ የደረሰበትን የክትባት ስምምነት 'እጅግ ጠቃሚ' በማለት ገልጸውታል።
''ስምምነቱ ለማድረግ ያሰብናቸውን ነገሮች ለማከናወን አንድ እርምጃ እንድንቀርብ ይረዳናል" ያሉ ሲሆን አክለውም '' ክትባቱ ሙሉ በሙሉ ደህንነቱ ሲረጋገጥ ብቻ ማከፋፈል እንጀምራለን'' ብለዋል።
ነገር ግን ኮሚሽነሯ ክትባቱ መቼ ለአባል አገራት መከፋፈል እንደሚጀምር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል። ''መጀመሪያ ከአውሮፓ የመድሀኒት ኤጀንሲ ፈቃድ ማግኘት አለበት፤ መጀመሪያ ላይ ማጠናቀቅ የሚገቡን በርካታ ስራዎች አሉ'' ብለዋል።
የአውሮፓ ሕብረት የጤና ኤጀንሲ እንዳስታወቀው የመጀመሪያ ዙር ክትባት በ27 አባል አገራት በሚቀጥለው የፈረንጆቹ ዓመት ይጀመራል።
''እንደሚመስለኝ የአዲሱ ዓመት የመጀመሪያዎቹ አራት ወራት ውስጥ ክትባቱን ለማከፋፈል እንችላለን'' ሲሉ ተደምጠዋል የአውሮፓ ተላላፊ በሽታዎች መከላከል ማዕከል ዳይሬክተሯ ከኤኤፍፒ የዜና ወኪል ጋር በነበራቸው ቆይታ።
ዳይሬክተሯ አክለውም በአውሮፓ ያለው የቫይረሱ ስርጭት ''በጣም በጣም አሳሳቢ'' ነው ያሉ ሲሆን ሁሉም ምልክቶች ወዳልሆነ መንገድ እያመራን እንደሆነ ይጠቁማሉም ብለዋል።
በርካታ የአውሮፓ ሕብረት አባል አገራት በሁለተኛ ዙር የኮሮረናቫይረስ ስርጭት ክፉኛ እየተጠቁ እንደሆነ ገልጸዋል። አብዛኛዎቹ አገራትም እንቅስቃሴ ላይ ገደብ መጣልና ሌሎች ይጠቅማሉ ያሏቸውን እርምጃዎች እየወሰዱ ነው።














