ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከሰማይ የተሠሩ አካባቢን የማይጎዱት አልማዞች
ከሰማይ ስለተሠሩ አልማዞች ሰምተው ያውቃሉ? ደህና፣ ካልሰሙ እንንገርዎት!
ዴል ቪንቼ ይባላሉ። የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያ ናቸው።
የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያው ዴል ቪንቼ -የአረንጓዴ ኢነርጂ ኩባንያው ኢኮትሪሲቲ መስራች ናቸው። ዴል ቪንቼ የፎረስት ግሪን ሮቨርስ እግር ኳስ ክለብ ሊቀመንበርም ናቸው።
እኚህ ግለሰብ ናቸው እንግዲህ ካርቦንን ከአየር በመሳብ ለአካባቢ የማይጎዱ ተስማሚ የሆኑ አልማዞችን ያዘጋጁት፡፡
የሰማይ አልማዝ (Sky Diamonds) ተብለው የሚጠሩ ሲሆን የተሰሩትም በእንግሊዟ ከተማ ስትራውድ ነው።
ሂደቱ የነፋስ እና የፀሐይ ኃይልን በመጠቀም ከከባቢ አየር ካርቦንን የሚያወጣ የሰማይ ማዕድን ማውጫ ተቋምን ይጠቀማል፡፡ የተሰበሰበ የዝናብ ውሃ እንደገና መጠቀምንም ያካትታል፡፡
ሂደቱ በተፈጥሮ ላይ ጉዳት የሚያደርሰውን ባህላዊ የአልማዝ ማዕድን ማውጣትን የሚገዳደር መንገድ ነው ብሏል ኩባንያው፡፡
ቡድኑ ከመሬት የሚገኘውን ዓይነት አልማዝ በአካልም በኬሚካልም የሚመስል ስኬታማ ዘዴ ለማግኘት ከአምስት ዓመታት በላይ ፈጅቶበታል። የአለም ዓቀፉ ማዕድናት፣ ጂሞሎጂ ተቋም የተመሰከረለትን አልማዝ ለመሥራት ሁለት ሳምንታት ይጠይቃል።
"ሁሉም ግብዓት ከሰማይ የሚገኝ ሲሆን አነስተኛ ወይም ዜሮ ካርቦን ሳይሆን ኔጋቲቭ ካርቦን ነው። ምክንያቱም የከባቢ አየር ካርቦንን ወደ አልማዝ እንቀይራለን" ያሉት ዴል ቪንቼ ናቸው።
"ከአሁን በኋላ ግዙፍ ጉድጓዶች በምድር ላይ መቆፈር አያስፈልገንም። አንዳንዶቹ ጉድጓዶች ከጠፈር ጭምር ይታያሉ። አልማዝ ለማግኘት መቆፈር አያስፈልገንም፣ ከሰማይ ብቻ እንሠራቸዋለን" ሲሉ አክለው ገልጸዋል።
"ይህንን እንደ 21ኛው ክፍለዘመን ቴክኖሎጂ እናየዋለን። የአየር ንብረት እና ሌሎች ዘላቂ ቀውሶችን ለመዋጋት ትክክለኛ አካሄድ ሲሆን እንደለመድነው እና ለመኖር እንደምንፈልገው እንድንኖር የሚያስችለን ነው" ብለዋል፡፡