የጊኒ ምርጫ፡ የ82 ዓመቱ ፕሬዚዳንት ለሶስተኛ ጊዜ ምረጡኝ እያሉ ነው

የፎቶው ባለመብት, AFP
ጊኒያውያን በአከራካሪ ሁኔታ ለሶስተኛ ጊዜ ፕሬዚዳንት ለመሆን የ82 ዓመቱ አልፋ ኮንዴ ለሚፎካከሩበት ምርጫ ድምጻቸውን መስጠት መጀመራቸው ተገልጿል።
ቀድሞውንም በተለያዩ የፖለቲካ አመለካካቶች የተከፋፈለችው የምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ጊኒ ባሳለፍነው አርብ ታጣቂዎች በአንድ ወታደራዊ ካምፕ ውስጥ ከፍተኛ አመራር መግደላቸው ደግሞ አገሪቱን ወደ ሌላ ውጥረት ውስጥ ከቷታል።
ፕሬዝዳንት አልፋ ኮንዴ ሕገመንግስቱን በማሻሻል ለሶስተኛ ዙር ውድድር ውስጥ ለመግባት ያደረጉትን እንቅስቃሴ በርካቶች ቢተቹትም እሳቸው ግን ትችቱን ወደ ጎን በማለት በምርጫው እየተወዳደሩ ይገኛሉ።
የአልፋ ኮንዴ ዋነኛ ተቀናቃኝ የሆኑት ሴሉ ዳሊያን ዲያሎ ሲሆኑ ከዚህ በፊት በምርጫው ሁለት ጊዜ ተሸንፈዋል።
ሁለቱ ተፎካካከሪዎች የምርጫ ቅስቀሳ ባደረጉባቸው አካባቢዎች ከጊኒ የብሄር ግጭት ተነስቶ የነበረ ሲሆን አገሪቱን ወደባሰ የእርስ በርስ ጦርነት እንዳይከታት ተፈርቶ ነበር።
መንግሥት በበኩሉ ከጎረቤት አገራት ጋር የሚያዋስኑ ድንበሮችን በሙሉ የደህንነት ስጋት አለ በማለት ዘግቷል።
በጊኒ 5.4 ሚሊዮን ሰዎች ለመምረጥ የተመዘገቡ ሲሆን አጠቃላይ የምርጫው ውጤት በርካታ ቀናት ሊፈጅ እንደሚችል ተገምቷል።
በአገሪቱ የምርጫ ሕግ መሰረት ከተወዳዳሪዎቹ መካከል አንዳቸው ለማሸነፍ ከ50 በመቶ በላይ ድምጽ ማግኘት የሚጠበቅባቸው ሲሆን ይህ የማይሆን ከሆነ ግን በሚቀጥለው ወር ሌላ ምርጫ የሚካሄድ ይሆናል።
ባሳለፍነው አርብ የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ላይ የታጠቁ ቡድኖች ኪንዲያ ውስጥ በሚገኝ አንድ ወታደራዊ ካምፕ በመግባት አንድ ወታደራዊ አዛዥ ገድለዋል።
አንዳንድ መገናኛ ብዙሀን የአገሪቱ መከላከያ ኃይል እርስ በርሱ ተከፋፍሏል የሚል ዘገባ ይዘው ቢወጡም መንግሥት ግን ሁሉም ነገር በቁጥጥር ስር ውሏል ጥቃት ፈጻሚዎቹም እየተፈለጉ ነው ብሏል።
አልፋ ኮንዴ በርካታ ዕድሜያቸውን ያሳለፉት በተቃዋሚ ፖለቲካኘነት ቢሆንም በአውሮፓውያኑ 2010 የተካሄደውን ምርጫ ካሸነፉ ወዲህ ግን የጊኒ ፕሬዝዳንት ቆይተዋል።
እሳቸው ሲያሸንፉም በአገሪቱ ታሪክ ከነጻነት በኋላ የተደረገ የመጀመሪያው ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ሆኗል።












