ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሜክሲኮ የቀድሞ መከላከያ ሚንስትር በአደንዛዥ እጽ ዝውውር ተከሰሱ
የቀድሞ የሜክሲኮ መከላከያ ሚንስትር ስልጣን ላይ ሳሉ አደንዥ እጽ በማዘዋወር እና በሕገ ወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ በማስመሰል ወንጀሎች ተከሰሱ።
ጀነራል ሳልቫዶር ዛፔዳ ሐሙስ ዕለት በአሜሪካ ሎስ አንጀለስ ከተማ በቁጥጥር ሥር ውለዋል።
ጀነራሉ እንደ ሄሮይን፣ ኮኬይን እና ማሪዋና ያሉ እጾችን ወደ አሜሪካ ሲያስገቡ ነበር ተብሏል።
አቃቤ ሕግ የቀድሞ መከላከያ ሚንስትር ኤች-2 የተባለው እጽ አዘዋዋሪ ቡድን እጅግ አደገኛ እንዲሆን እና አደንዛዥ እጾችን ወደ አሜሪካ እንዲያስገባ ድጋፍ ሲያደርጉ ነበር ይላል።
ከክሳቸው መካከል እንደ ኮኬይን እና ሄሮይን ያሉ አደንዛዥ እጾችን በአሜሪካ ለማከፋፈል መመሳጠር ይገኝበታል።
'ዘ ጋድፋዘር' በሚል ቅጽል ስም የሚታወቁት ጀነራሉ፤ ኤች-2 የተባለውን አደገኛ የሜክሲኮ እጽ አዘዋዋሪ ቡድን በመደገፍም ተወንጅለዋል።
ይህ ቡድን ሰዎችን በማሰቃየት፣ በመግደልም የሚወነጀል መሆኑን ዓቃቤ ሕግ አስታውቋል።
ዓቃቤ ሕግ፤ ጀነራሉ ከቡድኑ ከፍተኛ መሪ ጋር መነጋገራቸውን የሚያሳይ መረጃ አለኝ ብሏል።
ጀነራሉ ፍርድ ቤት ከመቅረባቸው በፊት ሊጠፉ ስለሚችሉ በቁጥጥር ስር እንዲቆዩ ተጠይቋል።
የቀድሞው መከላከያ ሚንስትር ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ ዓሥር ዓመትና ከዛም በላይ ሊታሰሩ ይችላሉ።
የሜክሲኮ መንግሥት ጀነራሉ በአሜሪካው ጸረ እጽ ተቋም ዲኤኤ ትዕዛዝ እንደታሰሩ ለቢቢሲ አረጋግጧል።
የአገረሪተቱ ፕሬዘዳንት አንድሬስ ማኑዌል ሎፔዝ "እስሩ በሜክሲኮ ዋናው ችግር ሙስና እንደሆነ ያሳያል" ብለዋል።
ሙስናን እዋጋለሁ በማለታቸው የተመረጡት ፕሬዘዳንት፤ ከሳቸው በፊት የነበረው አስተዳደር አደንዛዥ እጽ ዝውውርን ያልገታና ሙሰኛ እንደሆነ ይናገራሉ።
የቀድሞ መሪዎች ያለ መከሰስ መብት እንዲነሳና ተጠያቂ እንዲሆኑ ለማድረግም እየሞከሩ ነው።
የ72 ዓመቱ ጄነራል በሚንስትርነት ያገለገሉት እአአ ከ2012 እስከ 2018 ነው። ያኔ ፕሬዘዳንቱ ኤንሪኬ ፔና ኒትሮ ነበሩ።
በመከላከያው ከፍተኛ ሥልጣን እንዳለው ሰው አደንዛዥ እጽ ዝውውርን ለመግታት ይሠራሉ ተብሎ ቢጠበቅም፤ መንግሥት ከእጽ አዘዋዋሪዎች ጋር ይተባበር እንደነበር ይተቻል።
ከቀድሞው ፕሬዘዳንት የቅርብ አማካሪዎች አንዱ በቅርቡ በሙስና ተከሰው ከስፔን ወደ ሜክሲኮ ተወስደው ነበር።
ኤሚሊዮ ሎዞያ፤ ፔማክስ የተባለ የነዳጅ ኩባንያ ኃላፊ ሳሉ ከብራዚል የግንባታ ተቋም 10 ሚሊዮን ዶላር ጉቦ በመቀበል ተከሰዋል።
ጀነራሉ አሜሪካ ውስጥ በቁጥጥር ስር የዋሉ ብቸኛው ቀድሞ የሚክሲኮ ሚንስትር አይደሉም። ከዚህ ቀደም የቀድሞ የደህንነት ሚንስትር ጄናሮ ጋርሲያ ሉና ከእጽ አዘዋዋሪ ቡድን ጉቦ በመቀበል ተከሰዋል።
ኒው ዮርክ የፍርድ ሂደቱን እየተከታተሉ ያሉት የቀድሞ ባለሥልጣን የቀረበባቸውን ክስ አጣጥለዋል።