ኮሮናቫይረስ፡ ኮቪድ-19 የትራምፕ የቅርብ ሰዎችን እያዳረሰ ነው

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ስርጭት በዋይት ሐውስና በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዙሪያ ቀስ በቀስ እየተስፋፋ ነው።

የዋይት ሐውስ አማካሪ የሆኑት ስቴፈን ሚለር እና አንድ ከፍተኛ የጦር አዛዥ በቫይረሱ መያዛቸው ተሰምቷል።

ሚለር ላለፉት አምስት ቀናት ራሳቸውን ለይተው ውሸባ የገቡ ሲሆን ማክሰኞ እለት በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።

ጄነራል ማርክ ሚሌይ እና ሌላ ከፍተኛ ጦር ሹምም ባልደረባቸው የሆኑት አድሚራል ቻርልስ ሬይ በቫይረሱ መያዛቸው በምርመራ ከተረጋገጠ በኋላ ራሳቸውን ለይተው ውሸባ ገብተዋል።

ሌሎች ባለስልጣናትም "ለጥንቃቄ ሲባል" ራሳቸውን ለይተው ተቀምጠዋል።

ሚለር በሰጡት መግለጫ ላይ ራሳቸውን ለይተው ውሸባ ከገቡበት ቀን አንስቶ በየዕለቱ ተመርምረው ውጤታቸው ነጻ መሆናቸውን ያሳይ እንደነበር በመጥቀስ፣ ማክሰኞ እለት ግን በቫይረሱ መያዛቸው መረጋገጡን ተናግረዋል።

ባለቤታቸው የምክትል ፕሬዝዳንት ማይክ ፔንስ ቃል አቀባይ ስትሆን በግንቦት ወር ላይ በቫይረሱ ተይዛ አገግማለች።

በሐምሌ ወር የሚለር አያት በ97 ዓመታቸው ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ ሕይወታቸው አልፏል።

በወቅቱ ዋይት ሐውስ በእድሜ ጫና ምክንያት መሞታቸውን የሚገልፅ መግለጫ ሰጥቶ የነበረ ቢሆንም የሚለር አጎት ግን፣ የሞት ማስረጃ በማውጣት የሞቱት ከኮቪድ-19 ጋር ተያይዞ በመጣ የመተንፈሻ አካል ሕመም መሆኑን ይፋ አድርገዋል።

የፕሬዝዳንት ትራምፕ ንግግር ፀሀፊ የሆኑት ሚለር በስደተኞች ላይ የከረረ አቋም እንዳላቸው ይታወቃል።

የአሜሪካ የድንበር ጠባቂ ምክትል አዛዥ የሆኑት አድም ሬይ መጠነኛ የኮቪድ ምልክት እየታየባቸው መሆኑን ገልፀዋል።

ባለፈው ሳምንት ከእርሳቸው ጋር ስብሰባ ተቀምጠው የነበሩ አሁን ራሳቸውን ለይተው ውሸባ ገብተዋል።

በርግጥ ፔንታጎን እስካሁን አንድም አካል በቫይረሱ የመያዝ ምልክት አለማሳየቱን አስታውቋል።

አዳም ሬይ በቫይረሱ እንዴት ሊያዙ አንደቻሉ የተባለ ነገር የለም።

ከአስር ቀናት በፊት እኚህ የጦር መኮንን በዋይት ሐውስ የተዘጋጀ አንድ በዓል ላይ ተገኝተው የነበረ ሲሆን፣ ነገር ግን በቫይረሱ የተያዙት በበዓሉ ላይ ይሁን በሌላ ስፍራ የተባለ ነገር የለም ሲሉ ለፈረንሳዩ የዜና ወኪል ባለስልጣናት ተናግረዋል።

ከቅርብ ቀናት ወዲህ ፕሬዝዳንት ትራምፕና ሌሎች የቤተ መንግሥቱ ባለስልጣናት በኮቪድ-19 መያዛቸው ይታወቃል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ በኮቪድ-19 መያዛቸው ከተረጋገጠ በኋላ አብረዋቸው ይሰሩ የነበሩ ከፍተኛ የሪፐብሊካን ፓርቲ ሹማምንት በቫይረሱ ተይዘዋል።

ይህም ባለቤታቸውን ሚሌኒያ ትራምፕን ጨምሮ ረዳታቸው ሆፕ ሂክስ እና ሌሎች ሪፐብሊካን ሴናተሮችን ያካትታል።