ኖቤል ሽልማት፡ 'ሄፒታይተስ ሲ'ን ያገኙት ተመራማሪዎች ኖቤል ተሸለሙ

ሦስቱ ሳይንቲስቶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሽልማቱ ይፋ የተደረገው በስዊድን ስቶክሆልም፤ ካሮሊንስካ ተቋም በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነበር

የሄፒታይተስ ሲ ቫይረስን ያገኙት ሦስት ሳይንቲስቶች በሕክምና ዘርፍ የኖቤል ተሸላሚ ሆኑ። ሳይንቲስቶቹ እንግሊዛዊው ማይክል ሆግተን እና አሜሪካዊያኑ ሀርቪ አልተርና ቻርልስ ራይስ ናቸው።

የኖቤል ሽልማት ኮሚቴ እንዳለው፤ የሳይንቲስቶቹ ግኝት “በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ታድጓል”።

ቫይረሱ የኩላሊት ካንሰር ያስከትላል። ህሙማን የኩላሊት ንቅለ ተከላም ያስፈልጋቸዋል።

እአአ በ1960ዎቹ ደም የተለገሳቸው ሰዎች ባልታወቀ ህመም ሳቢያ ለሄፒታይተስ ይጋለጣሉ የሚል ስጋት ነበር።

የኖቤል ሽልማት ኮሚቴው ደም ልገሳ አደገኛ የነበረበት ወቅት እንደነበረ ጠቁሟል። አሁን ግን ለአደጋ የሚያጋልጥ የደም ልገሳን መቅረፍ መቻሉም ተጠቁሟል።

በተጨማሪም ፀረ-ቫይረስ መድኃኒቶች ማምረት ተችሏል።

ኮሚቴው "በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ህመሙን መፈወስ ተችሏል። ይህም ሄፒታይተስ ሲን ከዓለም ማስወገድ እንደሚቻል ተስፋ አጭሯል“” ብሏል።

ሆኖም ግን በየዓመቱ 70 ሚሊዮን ሰዎች በቫይረሱ ይያዛሉ። ከነዚህም 400,000 ይሞታሉ።

ገዳዩ ቫይረስ

ሄፒታይተስ ኤ እና ቢ የተገኙት በ1960ዎቹ ነበር።

በ1972 አሜሪካ ውስጥ ምርምር እያደረጉ የነበሩት ፕ/ር ሀርቪ አልተር ከሁለቱ ቫይረሶች በተጨማሪ ሌላም ገዳይ ቫይረስ መኖሩን ደረሱበት።

ብዙዎች ደም ከተለገሳቸው በኋላም ከህመማቸው አልተፈወሱም ነበር።

ተመራማሪው፤ ህመም ካለባቸው ሰዎች ለቺምፓንዚዎች ደም መሰጠቱ ለበሽታው ስርጭት ምክንያት መሆኑን ደርሰውበታል።

በወቅቱ ምንነቱ ያልታወቀው ህመም ‘ነን ኤ- ነን ቢ’ ወይም ኤም ቢም ያልሆነ ሄፒታይተስ ተብሎ ይጠራ ነበር።

ፕ/ር ማይክል ሆግተን በ1989 የቫይረሱን ዘረ መለ መለየት ችለዋል። ከዛም ቫይረሱ ሄፒታይተስ ሲ ተብሏል።

በዋሽንግተን ዩኒቨርስቲ ይሠሩ የነበሩት ፕ/ር ቻርልስ ራይስ ደግሞ በ1997 ለጥናቱ መደምደሚያ ሰጥተዋል።

ሄፒታይተስ ሲ ቫይረስ ላይ ዘረ መል አክለው በቺምፓንዚ ኩላሊት ውስጥ ከጨመሩ በኋላ በሽታው እንዴት እንደሚከሰት ደርሰውበታል።

የኖቤል ኮሚቴ ዋና ጸሀፊ ፕ/ር ቶማስ ፐርልማን፤ ከሦስቱ ሳይንቲስቶች መካከል ለሁለቱ ደውለው ኖቤል ማሸነፋቸውን እንደነገሯቸው ገልጸዋል።

“ሳነጋግራቸው ደስ ብሎኝ ነበር። ማሸነፋቸውን ሲሰሙ ተገርመዋል። ተደስተዋልም” ብለዋል።