ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡ በቫይረሱ የሞቱት የሮማኒያው ከንቲባ በምርጫ አሸነፉ
በኮሮናቫይረስ የሞቱት የሮማኒያው ከንቲባ በቅርቡ የተደረገውን ምርጫ በከፍተኛ ድምፅ አሸንፈዋል። 64 በመቶ የመራጮችንም ድምፅ ማግኘት ችለዋል።
በደቡባዊቷ ሮማኒያ በምትገኘው ግዛት ዴቬሴሉ ከንቲባ የነበሩት ኢዮን አሊማን ለሶስተኛ ጊዜም አሸንፈዋል።
ከሁለት ሳምንታት በፊት በመዲናዋ ቡካሬስት ህይወታቸው ያለፈው የቀድሞው ከንቲባ ስም ከተመራጮች ዝርዝር ውስጥ ነበር።
የተመራጮች ዝርዝር ቀድሞ በመታተሙ ስማቸውን ማስወገድ እንዳልተቻለም ባለስልጣናቱ አስታውቀዋል።
በዚህም ምክንያት የሞተ ሰው ከንቲባ ሆኖ እንደተመረጠም ተገልጿል።
ሌላ ምርጫ እንደሚደረግም ባለስልጣናቱ ለሮይተርስ የተናገሩ ሲሆን በርካታ የግዛቲቷ ነዋሪዎች የቀድሞ ከንቲባቸውን ቀብር በመጎብኘት ሃዘናቸውን በመግለፅ ላይ ናቸው።
በርካታ የመንደሪቷ ሰዎችም በመካነ መቃብሩ ተሰባስበው መታየታቸውን በማህበራዊ ሚዲያ የተጋሩ ቪዲዮዎች አሳይተዋል።
"ይህ የአንተ ድል ነው" ሲል አንድ ግለሰብ ሲናገር ተሰምቷል።
"እውነተኛ ከንቲባችን ነበር" በማለት ሌላ ግለሰብ ለአካባቢው የቴሌቪዥን ጣቢያ መናገሯን ሮይተርስ ዘግቧል።
"ሁሉንም የግዛቲቷን ነዋሪ በእኩል አይን ያይ የነበረ፤ ህግንም ያከብር ነበር። እንደሱ አይነት ከንቲባ መቼም አይኖረንም" ግለሰቧ ማለቷንም ሮይተርስ አስነብቧል።
የቀድሞ የባህር ኃይል አባል የነበሩት ኢዮን የግራ ክንፍ የሚያዘመው የሶሺያል ዲሞክራት ፓርቲ (ፒኤስዲ) አባል ነበሩ፤ በትናንትናው ዕለትም 57 አመታቸው ይሆን ነበር።
በከንቲባነታቸው በህዝባቸው በከፍተኛ ሁኔታ መወደዳቸውም በፓርቲያቸው ዘንድ ጥሩ ስም አስገኝቶላቸዋል።
ፓርቲያቸው በአሁኑ በተደረገው አገራዊ ምርጫ በተለያዩ ከተሞችና የምክር ቤቶች መቀመጫቸውን ለቀኝ ክንፍ አክራሪው ዩኤስ አር ፕላስ አሊያስና የአገሪቱን የመንግሥት ስልጣን በበላይነት ለተቆጣጠረው ሴንትሪስት ሊበራል አጥተዋል።
በበርካታ የአውሮፓ ህብረት አባል አገራት የፍትህ ስርአቱ እንዲሻሻልና የሰፈነው ሙስና እንዲቆም የሚጠይቁ ከፍተኛ የተቃውሞ ሰልፎችን ተከትሎም ነው ፒኤስዲ በርካታ መቀመጫዎችን በፖርላመንት በድምፅ እንዲያጣ የተደረገው።
የቀድሞ ከንቲባው ኢዮን ከሞቱ በኋላ በምርጫ ማሸነፍ በአገሪቷ የመጀመሪያው ክስተት አይደለም በጎሮጎሳውያኑ 2008 ኔኩላይ ኢቫስኩ የተባሉት ከንቲባም በጉበት በሽታ ከሞቱ በኋላ የቮይነስቲ ግዛት ከንቲባ ሆነዋል።