“ክትባት ቢገኝም ሁለት ሚሊዮን ሰዎች ሊሞቱ ይችላሉ”

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የዓለም ጤና ድርጅት ክትባት በስፋት ከመሰራጨቱ በፊት በቫይረሱ የሚሞቱ ሰዎች ሁለት ሚሊዮን ሊደርሱ ይችላሉ አለ።
የድርጅቱ የድንገተኛ ቡድን መሪ ዶ/ር ማይክ ራየን እንዳሉት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ካልተባበረ የሟቾች ቁጥር ሊጨምርም ይችላል።
ወረርሽኙ መሰራጨት ከጀመረ ወዲህ ወደ አንድ ሚሊዮን ሰዎች ሞተዋል። 32 ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ በበሽታው ተይዘዋል።
በአንዳንድ አገራት በሽታው እያገረሸ ሲሆን፤ አሜሪካ፣ ሕንድ እና ብራዚል ውስጥ በአጠቃላይ ከ15 ሚሊዮን በላይ ሰው ታሟል።
በሽታው ባገረሸባቸው የአውሮፓ አገራት ዳግመኛ የእንቅስቃሴ ገደብ የመጣል እቅድ አለ።
አውሮፓ ውስጥ በኮሮናቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ አሳሳቢ መሆኑን የተናገሩት ዶ/ር ማይክ፤ የእንቅስቃሴ ገደብ ከመጣል በፊት ምርመራ በማካሄድና በሽታው ካለባቸው ጋር ንክኪ ያላቸውን በመለየት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት መሞከር ያዋጣል ብለዋል።
ስለ ሟቾች ቁጥር ምን ተባለ?
ክትባት መሰራጨት ከመጀመሩ በፊት ሁለት ሚሊዮን ሰዎች ሊሞቱ ይችላሉ? የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ዶ/ር ማይክ “ሊሆን ይችላል” ብለዋል።
ለበሽታው የሚሰጠው ህክምና እየተሻሻለ መምጣቱ የሚሞቱ ሰዎችን ቁጥር መቀነሱን ቢናገሩም፤ ውጤታማ ክትባት ቢገኝም እንኳን የሟቾች ቁጥር ከሁለት ሚሊዮን እንደሚያልፍ አስረድተዋል።
መንግሥታት ኃላፊነታቸውን በመወጣት የሰዎችን ሕይወት እንዲታደጉም አሳስበዋል።
በተለያዩ አገራች ጥብቅ የጥንቃቄ እርምጃዎች እየተወሰዱ ነው።
ለምሳሌ በስፔን በሽታው በበረታበት ማድሪድ በከፊል እንቅስቃሴ የመግታት እቅድ ነበር። ተቃውሞ ስለገጠመው ተግባራዊ አልሆነም።
ፈረንሳይ ውስጥም የባርና ሬስቶራንት ተቀጣሪዎች ንግዳቸው እንዳይዘጋ ተቃውመዋል። ዩናይትድ ኪንግደም አዳዲስ የጥንቃቄ እርምጃዎች ወስዳለች።
እስራኤልም ንግድና በረራ ላይ ጥብቅ ገደብ ጥላለች።
በሌላ በኩል በሽታው የከፋባት አሜሪካ ንግድ ተቋሞች ላይ ተጥሎ የነበረውን ገደብ አንስታለች።
የተላላፊ በሽታዎች ባለሙያው ዶ/ር አንቶኒ ፋውቺ እንደሚሉት፤ አሜሪካ የወረርሽኙን የመጀመሪያ ዙር ስርጭት ገና አላለፈችም።














