በ2024 የመጀመሪያዋ ሴት ጠፈርተኛ ጨረቃን ትረግጣለች

የፎቶው ባለመብት, NASA
ናሳ እአአ በ2024 ወደ ጨረቃ በድጋሚ ለመጓዝ 28 ቢሊዮን ዶላር መድቧል። ‘አርቴሚስ’ የሚል ስያሜ የተሰጠው ጉዞ አንድ ወንድና አንድ ሴትን ያሳትፋል።
ጉዞው ከ1972 ወዲህ ሁለተኛው ሲሆን፤ ናሳ ጉዞውን በታቀደለት ጊዜ የሚያካሂደው ምክር ቤት 3.2 ቢሊዮን ዶላር ለመልቀቅ ሲስማማ ነው።
ጠፈርተኞቹ ጨረቃ ላይ የሚያርፉት እንደ አፖሎ ባለ ኦሪዮን በሚባል ሮኬት ነው።
የናሳ አስተዳዳሪ ጂም ብሪድንስትን እንዳሉት 28 ቢሊዮን ዶላሩ ለሮኬትና ሌሎችም ጠፈርተኞች ጨረቃን እንዲረግጡ የሚረዱ ቁሳ ቁሶች ይውላል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 600 ሚሊዮን ዶላር የፈቀደ ሲሆን፤ ናሳ ግን ለጉዞው ተጨማሪ ገንዘብ ይፈልጋል።
አርቴሚስ-1 የተባለው የጉዞው የመጀመሪያ ዙር በቀጣዩ ዓመት ይካሄዳል። ይህም የሙከራ በረራን ያካትታል።
የናሳ የሰዎች መንኮራኩር ዘርፍ ኃላፊ ካቲ ሉደርስ እንዳሉት አርቴሚስ-1 ለወር የሚቆይ ሙከራ ነው። አርቴሚስ-2 ላይ ሊገጥሙ የሚችሉ ችግሮችንም ይቀንሳል።
አርቴሚስ-3 ከ48 ዓመታት በኋላ የሰው ልጆች ጨረቃን የሚረግጡበት ፕሮጀክት ይሆናል።
ናሳ 967 ሚሊዮን ዶላር መድቦ የተለያዩ ተቋሞች የመንኮራኩር ዲዛይን እንዲሠሩ አድርጓል።
በምዕተ ዓመቱ ማገባደጃ ምርምር የሚደረግበትና ‘አርቴሚስ ካምፕ’ የተባለ ቋሚ መቆያ ይዘጋጃል ተብሎ ይጠበቃል። ይህም ሰዎች ዘለግ ላለ ጊዜ ስለ ጨረቃ እንዲመራመሩ ያግዛል።
ከጨረቃ ደቡባዊ ጫፍ ውሃ በማውጣት ወደ ጨረቃ ለሚጓዝ መንኮራኩር ነዳጅ የማመንጨት እቅድ አለ። ከተሳካ ከምድር ወደ ጨረቃ ለሚደረገው ጉዞ የሚወጣውን የነዳጅ ገንዘብ ያተርፋል።
ከዓመታት በፊት አፖሎ ወደ ጨረቃ ሲላክ 250 ቢሊዮን ዶላር ነበር የፈጀው።














