ኮሮናቫይረስ፡ በሕንድ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ቁጥር 5 ሚሊየን አለፈ

በሕንድ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር አምስት ሚሊየን ማለፉ ተገለፀ። ይህም አገሪቱን በአሜሪካ በመቀጠል በቫይረሱ ክፉኛ የተጎዳች እንድትሆን አድርጓታል።

በሕንድ በአንድ ቀን ብቻ እስከ 90 000 ሰዎች በኮቪድ-19 እየተያዙ ሲሆን ቫይረሱም በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ ነው ተብሏል።

እስካሁን ድረስ በአገሪቱ ከ80 ሺህ በላይ ሰዎች ሲሞቱ፣ በቫይረሱ ምክንያት በጽኑ ለታመሙ አልጋ እንዲሁም የኦክስጅን አቅርቦት እጥረት ተከስቷል።

በሕንድ የቫይረሱ ስርጭት እየተስፋፋ የመጣው በመጋቢት ወር ተጥሎ የነበረውን የእንቅስቃሴ ገደብ የምጣኔ ሃብቱን ለማነቃቃት በሚል ከተነሳ ወዲህ ነው።

ቫይረሱ ወደትንንሽ ከተሞች ከመሰራጨቱ በፊት እንደ ሙምባይና ደልሂ ያሉ ግዙፍ ከተሞችን ክፉኛ አጥቅቶ ነበር።

ሕንድ ምጣኔ ሃብቷን ክፍት ማድረግ በጀመረችበትና ሰዎች ወደ ስራ በተመለሱበት ወቅት የቫይረሱ ስርጭት እየተስፋፋ መምጣቱ ተስተውሏል።

ባለፉት ሳምንት ብቻ 600,000 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው በምርመራ ተረጋግጧል።

በሕንድ አሁን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 5,020,359 የደረሰ ሲሆን፣ ባለፈው 24 ሰዓታት ብቻ 90,123 መያዛቸው መታወቁ ተገልጿል።

በአገሪቱ የኦክስጅን ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ኦክስጅን አምራች ኢንደስትሪዎች ገልፀዋል።

በዚህ ወር ብቻ ሆስፒታሎችና የእንክብካቤ ማዕከላት 2,700 ቶን ኦክስጅን የተጠቀሙ ሲሆን፣ በሚያዚያ ወር ግን 750 ቶን ብቻ ነበር ፍጆታቸው ተብሏል።

የቫይረሱ ስርጭት እየጨመረባቸው ከሚገኙ የህንድ ከተሞች መካከል ማሃራሽትራ፣ ማድያ ፕራዴሽ፣ ጉጅራት፣ ራጃስታን፣ ቴሌንጋና፣ አንድሃራ ፕራዴሽ ናቸው።