የዛምቢያውን ፕሬዝደንት ጨምሮ በርካቶች የእድል ተምሳሌት በሆነው አሳ ሞት ሃዘን ላይ ናቸው

የፎቶው ባለመብት, EDGAR LUNGU/FACEBOOK
የዛምቢያው ፕሬዝደንት ኤድጋር ሉንጉ በአንድ የዛምቢያ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ውስጥ ለ20 ዓመታት የኖረ አሳ ሞት ምክንያት ሃዘን ላይ ናቸው።
የኮፐርቤልት ዩኒቨርሲቲ ማህብረሰብ አባላት በአሳው ሞት የተሰማቸውን ሃዘን እየገለጹ ሲሆን አሳውን ለማሰብ የሻማ ማብራት ስነ-ስርዓት ጭምር አካሂደዋል።
በደቡብ አፍሪካዋ አገር የአሳው መጠሪያ የነበረው ‘ማፊሲ’ የሚለው ቃል በትዊተር ላይ በበርካቶች ጥቅም ላይ እየዋለ ነው። ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት አሳው ለዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች እድል እና ሰላምን እንዲሁም የአእምሮ ሰላምን ይሰጥ ነበር ተብሏል።
ማፊሲ በቤምባ ቋንቋ “ትልቅ አሳ” ማለት ሲሆን፤ በዩኒቨርሲቲው ግቢ ውስጥ በሚገኝ የውሃ ገንዳ ውስጥ ቢያንስ ለ22 ዓመታት እንደኖረ የተማሪዎች ተወካይ የሆነው ሎውረንስ ካሶንዴ ይናገራል።
የአሳው አሟሟት ላይ ምርመራ እየተከናወነ መሆኑን እና ለአሳው የቀብር ስነ-ስርዓት እንደሚካሄድም ይሄው የተማሪዎች ተወካይ ለቢቢሲ ተናግሯል።
በዩኒቨርሲቲው የሁለተኛ ዓመት ተማሪ የሆነው ኤድዉን ናምቦ አሳው “የዩኒቨርሲቲው ልዩ መገለጫ” ነው በማለት የገለጸው ሲሆን፤ “ሲዋኝ ዝም ብሎ መመልከት በራሱ የአእምሮ እረፍት ይሰጥ ነበር። ከፈተና በፊት እና በአስቸጋሪ ጊዜ መጥቼ ማፊሲን እመለከት ነበር” ብሏል።
ፕሬዝደንት ሉንጉ በበኩላቸው “የአንድ አገር ኃያልነት እና የሞራል ልዕልና የሚገለጸው እንስሳቱ በሚያገኙት እንክብካቤ ነው” ሲሉ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል። ፕሬዝደንቱ ጨምረው፤ “ደማቅ አሸኛኘት ስለተደረገልህ ደስታ ተሰምቶኛል። እንናፍቅሃለን” ብለዋል።








