አሜሪካ፡ ሰባት ጊዜ በጥይት የተመታው አሜሪካዊ አባት ትራምፕን ማግኘት አልፈልግም አሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በፖሊስ በተደጋጋሚ በጥይት የተመታው ጥቁር አሜሪካዊ ጄኮብ ብሌክ አባት 'በልጄ ሕይወት የፖለቲካ ቁማር አልጫወትም' ብለዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ከሰዓታት በኋላ ዊስኮንሰን የምትገኘው ኬኖሻ ከተማን ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ጄኮብ ብሌክ በኬኖሻ ፖሊስ ነው በጥይት የተመታው። ይህን ተከትሎ በከተማዋና በሌሎች የአሜሪካ ክፍሎች ተቃውሞ ተቀስቅሶ ነበር።
ጄኮብ በሕይወት ይትረፍ እንጂ መራመድ እንደማይችል ሐኪሞች ተናግረዋል።
ትራምፕ የከተማዋን አስተዳዳሪዎች ያናግራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ከጉብኝቱ በፊት የጄኮብን በተሰቦች እንደማይገኙ ምክንያቱ ደግሞ ቤተሰቡ በጉብኝቱ ወቅት ጠበቃ እንዲኖር እንፈልጋለን ማለታቸው እንደሆነ ተናግረዋል።
ከሲኤንኤን ጋር ቆይታ የነበራቸው የጄኮብ አባት ጄኮብ ሲኒዬር፤ የልጃቸው ሕይወት ትራምፕን ከማግኘት በላይ ዋጋ እንዳለው ተናግረዋል።
"ፖለቲካ ውስጥ መግባት አልፈልግም። ይህ ጉዳይ የልጁ ጉዳይ ነው። ፎቶ ከመነሳት ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም።"
የከተማዋ አስተዳዳሪዎች በአካባቢው ዳግም ተቃውሞና ረብሻ እንዳይነሳ በመፍራት ፕሬዝደንቱ ኬኖሻን ባይጎበኙ ይሻላል ቢሉም ዶናልድ ዛሬ ከሰዓቱን መገኛዬ እዚያ ነው ብለዋል።
ትራምፕ ዴሞክራቶቹ የዊስኮንሰን ሃገረ ገዥና የከተማዋ ከንቲባ ሰላም ማስከበር አልቻሉም ሲሉ ይወቅሳሉ።
ትራምፕ በመጪው ኅዳር ለሚከናወን የአሜሪካ ምርጫ ዋነኛ አጀንዳቸው አድርገው የያዙት ሕግና ሥርዓትን ማስከበር እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይደመጣሉ።
በቅርቡ ደግሞ የ29 ዓመቱ ጄኮብ ብሌክ በነጭ ፖሊስ ሰባት ጊዜ በጥይት መመታቱን ተከትሎ በርካታ ከተማዎች ተቃውሞ ሲያስተናግዱ ነበር።
የጄኮብ አባት ከትራምፕ ጋር በመጨባበጥ ልጃቸውን ላይ የደረሰውን ጥቃት በፖለቲካ ለመሸፈን እንደማይሞክሩ ነው ለሲኤንኤን የተናገሩት።
"ልጄ ከጥቂት ሳምንታት በፊት እየተሯሯጠ ከልጆቹ ጋር ይጫወት ነበር። ስልክ ደውሎልኝ እያወራን እንሳሳቅ ነበር። አሁን ግን እግሮቹን እንኳ ማንቀሳቀስ አይችልም።"
ጄኮብ ብሌክን በጥይት በተደጋጋሚ መቶታል የተባለው ነጩ ፖሊስ ረስተን ሼስኪ ምርመራ እየተካሄደበት ስለሆነ በግዳጅ እረፍት እንዲወጣ ተደርጓል።
ምንም እንኳ ትራምፕ የተጎጂውን ቤተሰብ አያግኙ ከተማዋን ይጎበኛሉ ተብሏል። ፕሬዝደንቱ በሰሞኑ ግርግር የወደሙ ንበረቶችን ይጎበኛሉ ይላል ከቤተ መንግሥታቸው የተለቀቀው መረጃ።
በግርግሩ ወቅት ዘረኝነትን ተቃውመው ሰልፍ ከወጡ ሰዎች ጋር የትራምፕ ደጋፊዎች ተጋጭተዋል። በወቅቱ ሁለት ሰዎችን ገድሏል የተባለ አንድ ታዳጊን ድርጊት ፕሬዝደንቱ መከላከላቸው እያስወቀሳቸው ነው።
ያለፉት ወራት አሜሪካ በፀረ-ዘረኝነት ተቃውሞ ከጥግ እስከ ጥግ የተናጠችበት ነው። ተቃውሞቹ የተቀሰቀሱት ጥቁር አሜሪካዊው ጆርጅ ፍሎይድ በፖሊስ እጅ ከተገደለ በኋላ ነው።














