ጋምቤላ ፡ ባለስልጣናት ላይ ጥቃት የማድረስ ሙከራ መክሸፉን ፖሊስ አስታወቀ

ከሰሞኑ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ላይ የግድያ ሙከራ የፈጸሙ ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የክልሉ ከፍተኛ ባለሥልጣን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድርን፣ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር፣ አፈጉባኤ፣ ምክትል አፈጉባኤ፣ የክልሉ የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ ባለስልጣናትን ሊገድሉ ሙከራ አድርገዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቋል።
ነሐሴ 22/2012 ነበር በበክልሉ አኙዋ ዞን ጆር ወረዳ ከፍተኛ አመራሮቹ ከማኅበረሰቡ ጋር ለመወያየት ወደ ስፍራው ያቀኑት።
የጋምቤላ ክልል ምክትል የፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ቱት ኮር ለቢቢሲ እንደገለጹት በርዕሰ መስተዳድሩ የሚመራው የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ቡድን በጎንግ ወረዳ ያደረገውን ጉብኝት በማጠናቀቅ ነበር ወደ ጆር ወረዳ ያቀናው።
የጉብኝቱ ዓላማም አካባቢውን ለመጎብኝት እና ያለውን የጎርፍ ሁኔታ በማየት ከአካባቢው ሽማግሌዎች እና ወጣቶች ጋር ለመወያየት እንደነበረ ተናግረዋል።
በጆር ወረዳ በሚገኘው ምክር ቤት ውስጥ በተደረገው ውይይት ላይ የተደራጁ ወጣቶች በክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት ላይ ጥቃት ለመፈጸም ሙከራ ማድረጋቸውን አረጋግጠዋል።
ምክትል የፖሊስ ኮሚሽነሩ እንዳሉት ይህ ጥቃት ቀደም ሲል ጀምሮ ዝግጅት የተደረገበት እንደነበር አመልክተው፤ የግድያ ሙከራው በከፍተኛ አመራሮቹ ጠባቂዎች አማካእነት መክሸፉን ተናግረዋል።
ከጥቃቱ ሙከራ ጋር በተያያዘም 19 የሚሆኑ ተጠርጣሪዎች ወዲያውኑ በጸጥታ አካላት ቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ለቢቢሲ ተናግዋል።
ጥቃቱን ለመፈጸም መሞከራቸው የተነገረውና በቁጥጥር ስር የዋሉት ተጠርጣሪዎች መነሻቸው ከጋምቤላ ከተማ ነበር ያሉት አቶ ቱት ከእነርሱ ጋር አንድ የአሜሪካ ዜግንት ያለው ዶክተርም በቁጥጥር ስር መዋሉን ጠቅሰዋል።
አሜሪካዊው ወጣቶቹን ከማደራጀት ባለፈ በስሙ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ማምጣቱን እና ወጣቶቹ እጅ ላይ የተለያየ መጠን ያለው ገንዘብ መያዙንም ጠቁመዋል።
ተጠርጣሪዎቹ እጅ ላይ ድምጽ አልባ መሣሪያን ጨምሮ አንድ ሕገ ወጥ ሽጉጥ በቁጥጥር ስር መዋሉን አመልክተው ተጨማሪ ምርመራ እየተደረገ ነው።
ተጠርጣሪዎቹ ጥቃቱን ለማድረስ በታሰበበት አዳራሽ ውስጥ ድንገተኛ ግጭት በመፍጠር አቅጣጫ ለማስቀየር ሙከራ ማድረጋቸውን የተናገሩት ምክትል ኮሚሽነሩ፤ በወቅቱ የከፍተኛ አመራሮቹ ጠባቂዎች ክስተቱን ለመቆጣጠር ወደ ሰማይ ጥይት መተኮሳቸውን ተናግዋል።
ስለጉዳዩ ቀደም ሲል መረጃ እንደነበራቸውና አስፈላጊው ክትትል ሲደረግ እንደነበር የገለጹት አቶ ቱት ተጠርጣሪዎቹ ርዕሰ መስተዳድሩ ከጋምቤላ ከተማ ሳይወጡ ጥቃቱን የመፈጸም ዓላማ ነበራቸው ብለዋል።
"ከጋምቤላ ብዙ ብዙ ማስፈራሪያ እና ዛቻ ነበር። እነሱን መነሻ አድርገን ብዙ መረጃዎች ነበሩን። የይህን መሠረት አድርጎ ነው የማክሸፍ ሥራው የተሰራው" ብለዋል።
የተጠርጣሪዎቹ ዓላማ "ርዕሰ መስተዳድሩ ላይ እርምጃ መውሰድ እና በኃይል ከስልጣን ለማሰወገድ ነበር" ብለዋል።
እስካሁን በቁጥጥር ስር የዋሉት ሰዎች ቁጥር 25 መድረሱን ጠቁመው እየተፈለጉ ያሉ ሌሎች ሰዎች እንዳሉም ጨምረዋል ምክትል ኮሚሽነሩ ለቢቢሲ ተናግረዋል።።
በተጨማሪም ተጠርጣሪዎቹ ቅዳሜ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተከትሎ ምርመራው ዛሬ መጀመሩን እና ነገ ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ አስታውቀዋል።
አካባቢው አሁን ሠላማዊ መሆኑን ጠቁመው ምንም የተለየ ነገር አለመኖሩን እና ውይይት እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።














