ጥንታዊ መገልገያ ፡ ከፈረስ አጥንት የተሠሩ የጥንታዊ ሰው መገልገያዎች ተገኙ

ከፈረስ አጥንት የተሠሩ የጥንታዊ ሰው መገልገያዎች ተገኙ

የፎቶው ባለመብት, UCL INSTITUTE OF ARCHAEOLOGY

በአውሮፓ የቅሪተ አካል ጥናት (አርኪዎሎጂ) ዘርፍ ጥንታዊ የተባሉ ከአጥንት የተሠሩ መገልገያዎች ተገኙ።

መገልገያዎቹ በአውሮፓውያኑ በ1980ዎቹ እና 90ዎቹ አካባቢ ሰዎች ጥለውት የወጡት ምዕራብ ሰሴክስ አካባቢ ነው የተገኙት።

ጥንታዊ ሰዎች ይጠቀሙባቸው የነበሩት መሣሪያዎች የተዘጋጁት ከፈረስ አጥንት ነበር።

ፈረሱ ታርዶ ስጋው ለምግብነት ከዋለ በኋላ አጥንቱ መገልገያ ለመሥራት ውሏል።

በአካባቢው የተገኘው እንስሳ ቅሪተ አካል ዙርያ የነበረው የድንጋይ ክምር፤ መሣሪያውን ለማዘጋጀት ቢያንስ ስምንት ሰዎች መሳተፋቸውን ያሳያል።

በአካባቢው ወጣት ወይም በእድሜ የገፉ የማኅበረሰቡ አባላት እንደነበሩም ተመራማሪዎች ደርሰውበታል።

በብሪታኒያ በተካሄደው ቁፋሮ ወደ መቶ የሚጠጉ የድንጋይ መገልገያዎችና ወደ 500 ሺህ ዓመታት ገደማ ያስቆጠሩ የእንስሳት ቅሪተ አካሎች ተገኝተዋል።

መገልገያዎቹ የዘመናዊ ሰው እንዲሁም የኒያንደርታልስ ቅድመ ዝርያ በነበሩት ሆሞ ሄይድልበርገንሲስ እንደተሠሩ ይታመናል።

በቁፋሮ የተገኘው የሰው ቅልጥም ቅሪተ አካል ከብሪትን የሰው ቅሪተ አካሎች በእድሜ ትልቁ ነው።

የምርምር ሂደቱን የመሩት ዶ/ር ማቲው ፖፕ “አሁን ዝርያው የጠፋ ማኅበረሰብ የኖረበትን አካባቢ እንዳለ ማግኘት ትልቅ እድል ነው” ብለዋል።

ተቀራርበው ይኖሩ የነበሩ ጥንታዊ ሰዎችን ማኅበራራዊ ትስስር መገንዘብ እንደቻሉም አክለዋል።

ተመራማሪው እንደሚናገሩት፤ ፈረስ እንዴት ወደዛ አካባቢ እንደደረሰ አልታወቀም።

“ፈረሶች ጥብቅ ማኅበራዊ ትስስር ያላቸው እንስሳት ናቸው። ስለዚህም ቅሪተ አካሉ የተገኘው ፈረስ የመንጋ አባል እንደነበረ መገመት ይቻላል። ግን በአንዳች ምክንያት ከመንጋው ተለይቶ እዛ አካባቢ ሕይወቱ አልፏል።”

ምናልባትም ፈረሱ እየታደነ ነበር የሚል መላ ምት አለ።

የፈረስ ቅሪተ አካል ላይ የተሠራው ጥናት፤ ፈረሱ ከምግብነት ባሻገር አጥንቱ መገልገያ ለመሥሪያነትም እንደዋለ ይጠቁማል።

የለንደን ዩኒቨርስቲ ኮሌጁ ተመራማሪ ሳይመን ፓርፊት፤ “በሰው ልጅ ዝግመተ ለውጥ ሂደት የተገኙ እድሜ ጠገብ ከድንጋይ ያልተዘጋጁ መገልገያዎች ናቸው” ብለዋል።

ዶ/ር ሲልቪያ ቤሎ በበኩላቸው፤ ግኝቱ ጥንታዊ ሰው ከአንድ ቁስ እንዴት ሌላ ቁስ ማዘጋጀት እንደሚቻል መገንዘቡን ይጠቁማል ሱሉ አስረድተዋል።

በአዕምሮ፣ በማኅበራዊ ትስስር እንዲሁም በባህልም የመጠቁ መሆናቸውን እንደሚያሳየም አክለዋል።

ተመራማሪዎቹ ቅሪተ አካሉን ባገኙበት ስፍራ አቅራቢያ ከ30 እስከ 40 የሚሆኑ ሰዎች ይኖሩ እንደነበር ገምተዋል። ምናልባትም አደኑን ተቀላቅለው ፈረሶች ገድለው ሊሆን እንደሚችል መላ ምት ተቀምጧል።

ሰዎች ከፈረስ አጥንት መቅኒና ፈሳሽ ያገኙ እንደነበርም መረጃ ተገኝቷል።

ተመራማሪዎቹ እንደሚሉት፤ አደን እና እንስሳትን ማረድ ለጥንታዊ ሰዎች ማኅበራዊ ክንውኖች ነበሩ።