በአንድ ቀን የተወለዱ ልጆች በስሟ እንዲጠሩ ስለተደረገላት አትሌት ያውቃሉ?

ሞሮኳዊት አትሌት ናዋል ኤል ሞውታዋኬል

ናዋል ኤል ሞውታዋኬል ሞሮኳዊት አትሌት ናት። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር ነሐሴ 8፣ 1984 በሎስ አንጀለስ ኦሎምፒክ ድል ተቀዳጅታለች።

ማሸነፏ እጅግ ያስደሰታቸው ሞሮኳዊው ንጉሥ ሐሰን በእለቱ የተወለዱ ሴቶች ባጠቃላይ ናዋል ተብለው እንዲጠሩ ውሳኔ አስተላልፈዋል።

ሰሞኑን 36ኛ ዓመት ልደታቸውን የሚያከብሩ የሞሮኮ ሴቶች ስማቸው ናዋል የመሆን እድሉ ሰፊ ነው።

ናዋል በኦሎምፒክ ወርቅ ሜዳልያ ያገኘች የመጀመሪያዋ ሞሮኳዊት ናት። በ400 ሜትር የመሰናክል ዝላይ ያሸነፈች የመጀመሪያዋ ሴትም ናት።

በሎስ አንጀለሱ ኦሎምፒክ ላይ የተገኘች ብቸኛዋ ሞሮኳዊት ሴት ናዋል ነበረች። በኦሎምፒክ ታሪክ ድል የተቀዳጀች የመጀመሪያዋ ሴት አረብ አፍሪካዊትም ናት።

የውድድሩ ተካፋይ የነበረው ሰዒድ አዊታ በ500 ሜትር ሩጫ ያሸነፈው ምናልባትም በናዋል ድል ተነሳስቶ ይሆናል።

“ስለውድድሩ ሳስብ ሌሊቱን በሙሉ እንቅልፍ አልወሰደኝም”

ናዋል ከውድድሩ አንድ ቀን በፊት ሲያቃዣት ነበር። መሰናክል ዘላ አንዳች ጉድጓድ ውስጥ እንደምትገባ ይሰማት እንደነበር ታስታውሳለች።

“በጣም ፈርቼ ነበር። ብቸኛዋ ሞሮኳዊት ሴት ስለነበርኩ ሁሉም የቡድኑ አባላት ተስፋ ጥለውብኝ ነበር።”

ውድድሩን ከማሸነፏ በፊት የነበረውን ምሽት እንዲህ ታስታውሰዋለች።

“ስለ ውድድሩ ሳስብ ሌሊቱን በሙሉ እንቅልፍ አልወሰደኝም ነበር። ሲያቃዠኝ፣ ሲያልበኝ ስለነበር መተኛት አልቻልኩም። ዝግ ብዬ ስሮጥ ይታየኝ ነበር።”

በችሎታዋ አምና በውድድሩ ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ ትፈልግ ነበር።

“ያሰብኩት ከመጨረሻዎቹ ስምንት ተወዳዳሪዎች አንዷ እንደምሆን ነበር። አሰልጣኞቼ እንደማሸንፍ ስላሰቡ በራሴ እንድተማመን ደጋግመው ይነግሩኝ ነበር።”

ናዋል እና አሰልጣኞቿ ከመጨረሻው ውድድር በፊት የሷና የተፎካካሪዎቿን ያለፉ ውድድሮች ቪድዮ ይመለከቱ እንደነበር ታስታውሳለች። የሷን ደካማና ጠንካራ ጎኖች ከተፎካካሪዎቿ ጋር ያነጻጽሩም ነበር።

“ላሸንፍ ስለምችል ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ጠንካራ መሆን እንዳለብኝ ይነግሩኝ ነበር” ትላለች።

ናዋል እንደምታሸንፍ ማመኗ የስኬቷ ሚስጥር ነበር። እራሷን “ያንቺ ጊዜ ነው። ድል ሊያመልጥሽ አይገባም” እያለችም ነበር።

የናዋል አሜሪካዊት ጓደና ጁዲ ብራውንም የውድድሩ ተሳታፊ ነበረች። በእርግጥ የውድድሩ ተመልካቾች የ22 ዓመቷ ናዋል ደጋፊ አልነበሩም።

ጋዜጠኞች ውድድሩን በአንክሮ ይከታተላሉ ነበር።

ውድድሩ በይፋ ከመከፈቱ በፊት ናዋል በስህተት የጀመረች መስሏት ተደናግጣ ነበር። ኋላ ላይ ግን ተረጋጋች።

“የመጀሪያውን፣ ሁለተኛውንና ሦስተኛውን መሰናክል በግራ እግሬ ዘለልኩ። ከዛ እስከ መጨረሻው ድረስ ቀኝና ግራ እግሬን መለዋወጥ ጀመርኩ።”

ተፎካካሪዎቿን በቅርብ ርቀት ማየት ስላልቻለች ግራ ተጋብታ እንደነበር ታስታውሳለች።

“ሌሎቹ ሯጮች የት ገቡ? ብዬ አሰብኩ። ለካ በጣም ቀድሜያቸዋለሁ። የመጨረሻውን ነጥብ ከማለፌ በፊት እኔ ብቻ እያለፍኩ መሆኑን ለማረጋገጥ ወደ ግራና ቀኝ ተመለከትኩ።”

ናዋል ኤል ሞውታዋኬል

“አባቴ በቦታው ባለመኖሩ ከፍቶኝ ነበር”

ናዋል ወርቅ ስታገኝ ጓደኛዋ ጁዲ ብራውን ብር አግኝታለች።

“ሳሸንፍ በጣም ነው ደስ ያለኝ። ግን አባቴ በቦታው ባለመኖሩ ከፍቶኝ ነበር። ሁሌም ይደግፈኝ የነበረው አባቴ ከውድድሩ ከወራት በፊት ሕይወቱ አልፏል።”

የናዋል ቤተሰቦች ስፖርት ወዳጅ ናቸው። አባቷ የጁዶካ ተጫዋች (እንደ ማርሻል አርት አይነት ውድድር) እናቷ ደግሞ መረብ ኳስ ተጫዋች ነበሩ።

ናዋል ህልሟን እንድታሳካ ቤተሰቦቿ ይደግፏት ነበር።

“ማሸነፌ ለአገሬ ትልቅ ዜና ነበር። ማንም ያልጠበቀው ድል ነው። አንዲት ታዳጊ ሞሮኳዊት ከምርጥ አትሌቶች ጋር ተፎካክራ አሸንፋ ወርቅ ታገኛለች ብሎ ማንም አላሰበም። በልቤና በአዕምሮዬ እስከወዲያኛው የሚኖር ታሪካዊ ቅጽበት ነው።”

የናዋል ድል በወግ አጥባቂ አረብና ሙስሊም አገሮች ለሚኖሩ ብዙ ሴቶች በር ከፍቷል።

“ከዛ በኋላ ብዙ ሞሮኳዊ ሴቶች አሸንፈዋል። በአልጄሪያ፣ ቱኒዚያ፣ ግብፅ እና ባህሬን የሚኖሩ ሴቶችም እንዲሁ። በኦሎምፒክስ ላይ ሴቶች አሳትፈው የማያውቁ አገሮች፤ ሴቶችን ለተሳትፎ ብቻ በቡድናቸው ከማካተት አልፈዋል። ሴቶች የሚካተቱት ለተሳትፎ ሳይሆን ለማሸነፍ ሆኗል” ትላለች አትሌቷ።