ኮሮናቫይረስ፡በሕንድ በኮቪድ ጊዜያዊ ሆስፒታል ባጋጠመ የእሳት አደጋ ቢያንስ አስር ህሙማን ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በደቡብ ምስራቅ ሕንድ ቪጃያዋዳ በሚገኝ የኮቪድ-19 ጊዜያዊ ሆስፒታል በተነሳ እሳት ቢያንስ አስር ህሙማን መሞታቸው ተገለፀ።
እሳቱ ህሙማኑ ሕክምና በሚከታተሉበት 'ስዋርና ፓላስ' ጊዜያዊ የኮቪድ ማዕከል እሁድ ጠዋት መነሳቱ ተገልጿል።
ባለሥልጣናት እንዳሉት እሳቱን በግማሽ ሰዓት ውስጥ መቆጣጠር የተቻለ ሲሆን፤ ከአደጋው የተረፉ ህሙማንም ወደ ሌላ ሆስፒታል ተዛውረዋል።
የቪጃያዋዳ ፖሊስ ኮሚሽነር ቢ ስሪኒቫሱሉ፤ በሆስፒታሉ ውስጥ ከ30 በላይ ሰዎች እንደነበሩ ገልፀው የሟቾቹ ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ናርንድራ ሞዲም ተጎጂዎችን በፀሎታቸው እንደሚያስቧቸው እና አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደረግላቸው ከሚመለከታቸው ጋር መነጋገራቸውን በትዊተር ገፃቸው አስፍረዋል።
የአንድራ ፓራዲሽ ግዛት ሚኒስትር ጃጋን ሞሃን የተጎጂ ቤተሰቦች 66 ሺህ 670 ዶላር (5 ሚሊየን ሩፒስ) ካሳ እንደሚሰጣቸው አስታውቀዋል።
የአደጋውን ምክንያት ለማጣራትም ምርመራ እየተካሄደ ነው ተብሏል።
በቀናት ውስጥ በኮቪድ-19 የህክምና ማዕከል ውስጥ አደጋው ሲከሰት ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
ሐሙስ እለት በአህሜዳባድ በሚገኝ የኮቪድ -19 ሆስፒታል ውስጥ በፅኑ ሕሙማን ክፍል በተነሳ የእሳት አደጋ ስምንት ህሙማን መሞታቸው ይታወሳል።
እንደ ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ ሕንድ በቫይረሱ በተያዙ ሰዎች ቁጥር በዓለማችን ካሉ አገራት በሦስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠች ሲሆን እስካሁን ከ2.1 ሚሊየን በላይ ሰዎች በበሽታው ተይዘዋል።
ከ43 ሺህ የሚበልጡ ሰዎች ደግሞ በበሽታው ሳቢያ ሕይወታቸው አልፏል።
እሁድ ዕለት ብቻ 64 ሺህ ተጨማሪ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል። ይህም በአንድ ቀን የተመዘገበ ከፍተኛው ቁጥር ነው ተብሏል።












