ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሱዳን ወደ ዳርፉር ተጨማሪ ወታደሮች ልትልክ ነው
ሱዳን ተጨማሪ ወታደሮችን መረጋጋት ወደ ራቀውና በቅርቡ ግጭት ወደተቀሰቀሰበት የዳርፉር ግዛት ልትልክ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ አስታወቁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወታደሮቹ በዚህ የእርሻ ወቅት ዜጎች ተረጋግተው ግብርናቸው ላይ እንዲያተኩሩ ጥበቃ ያደርጋሉ ብለዋል።
ቅዳሜ እለት ማንነታቸው ያልታወቀ ታጣቂዎች 60 ሰዎችን የገደሉ ሲሆን፣ ከዚያ በፊት ደግሞ 20 ሰዎች መሞታቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል።
እንደ ተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (OCHA) መረጃ ከሆነ በርካታ ቤቶች ተቃጥለዋል፣ የገበያ ሥፍራዎችና ሱቆች ተዘርፈዋል።
"በዳርፉር ግዛት የሚታየው የግጭት መስፋፋት ዜጎች እርሻቸውን ትተው እንዲሰደዱ፣ ለህይወትና ለንብረት መጥፋት እንዲሁም ለሰብዓዊ እርዳታ ፍላጎት መጨመር ሰበብ ሆኗል" ይላል የድርጅቱ መግለጫ።
እስካሁን ድረስ የትኛውም ቡድን ለጥቃቱ ኃላፊነቱን አልወሰደም።
ዳርፉር ላለፉት ሁለት አስርታት በግጭት ስትታመስ የነበረች ሲሆን፤ ውጊያው ይካሄድ የነበረው ደግሞ ለቀድሞው የሱዳን ፕሬዝዳንት ኦማር አል በሽር ታማኝ በሆኑ ኃይሎችና በአማፂያን መካከል ነበር።
እንደ ተባበሩት መንግሥታት መረጃ ከሆነ በዳርፉር ግጭት 300,000 ያህል ሱዳናውያን ሞተዋል ሁለት ሚሊዮን ደግሞ ተፈናቅለዋል።
አል በሽር በዳርፉር ለፈፀሙት የዘር ማጥፋት ወንጀል በዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ይፈለጋሉ።
የ76 ዓመቱ አልበሽር ባለፈው ሳምንት ካርቱም በሚገኝ ፍርድ ቤት ቀርበው ወደ ሥልጣን በመጡበት የመፈንቅለ መንግሥት ጉዳይ ተከስሰዋል።
ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ ሞት ይጠብቃቸዋል ተብሏል።
የቀድሞው የሱዳን ፕሬዝዳንት አል በሽር በሙስናም ተከስሰው ጉዳያቸው እየታየ ይገኛል።