አሜሪካና ቻይና የሚወዛገቡባት ተመራማሪ በሳን ፍራንሲስኮ ቆንስላ ተደብቃለች ተባለ

ቪዛ በማጭበርበር እና ከመከላከያ ሠራዊት ጋር ያላትን ትስስር በመደበቅ የተጠረጠረች ቻይናዊት በአሜሪካ ሳን ፍራንሲስኮ ቆንስላ መደበቋ ተገለጸ።

የአሜሪካ ዐቃቤ ሕግ እንደሚለው፤ ግለሰቧ ቻይና ወታደራዊ ሳይንቲስቶችን ወደ አሜሪካ ለማስገባት የምታደርገው ጥረት አንድ አካል ናት።

ትላንት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሂውስተን፤ ቴክሳስ የሚገኝ የአሜሪካ ቆንስላ እንዲዘጋ መወሰናቸው ይታወሳል። ቆንስላው የአሜሪካን አዕምሯዊ ንብረት ሰርቋል ሲሉም ትራምፕ ከሰዋል።

ቻይና ቆንስላዋ መዘጋቱን እና ሳይንቲስቶቿ ላይ የሚደርሰውን ጫና ኮንናለች። የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ቃል አቀባዩ ዋንግ ዌንቢን፤ አሜሪካ ሰበብ ፈልጋ ቻይናውያን ተመራማሪዎችን እያንገላታች ነው ብለዋል።

ትራምፕ የሂውስተኑን ቆንስላ ካዘጉ በኋላ ሌሎችም የቻይና ቆንስላዎች እንደሚዘጉ አስፈራርተዋል።

ላለፉት ጥቂት ወራት አሜሪካ እና ቻይና በተለያዩ ጉዳዮች ሰበብ ሲወዛገቡ ነበር። የኮሮናቫይረስ ጉዳይ እንዲሁም ቻይና ሆንግ ኮንግን በተመለከተ ያወጣችው አዲስ ሕግ እያጨቃጨቃቸው ይገኛል። የንግድ ግንኙነታቸውም ሌላው የግጭት መነሻ ሆኗል።

የሳን ፍራንሲስኮው ክስ ምንድን ነው?

በሳን ፍራንሲስኮ ፍርድ ቤት የቀረበው ክስ እንደሚያሳየው፤ ጁዋን ታንግ የተባለችው ቻይናዊት በካሊፎርንያ ዩኒቨርስቲ የሥነ ሕይወት ተመራማሪ ስትሆን፤ በቻይና ወታደራዊ ተቋም አልሠራሁም ብላ ዋሽታለች።

ሆኖም የወታደር መለያ አድርጋ የሚያሳዩ ፎቶዎች ተገኝተዋል። ከቻይና ሕዝብ ነጻነት ሠራዊት ጋር ትስስር እንዳላት የሚያሳዩ መረጃዎችም እንዳሉ ተገልጿል።

ምርመራ በሚካሄድበት ወቅት ቻይናዊቷ ሳን ፍራንሲስኮ ወደሚገኝ የቻይና ቆንስላ መግባቷም ተዘግቧል። ቆንስላው ወታደሮች አሜሪካ ውስጥ እንዳይከሰሱ ከለላ እንደሚሰጥም ተገልጿል።

ዐቃቤ ሕግ እንደሚለው፤ ቻይና ወታደራዊ ሳይንቲስቶችን ወደ አሜሪካ ስትልክ የመጀመሪያዋ አይደለም።

ባለፉት ሳምንታት ሁለት ተመራማሪዎች ካሊፎርንያ ውስጥ የታሰሩ ሲሆን፤ መከላከያ ተቋም ውስጥ ሠርተን አናውቅም ብለው ዋሽተዋል ተብሏል።

በቻይና ቆንስላ ምን እየተከናወነ ነው?

ሂውስተን የሚገኘው ቆንስላ የተዘጋው ጊቢው ውስጥ ያሉ ሰዎች ቆሻሻ መጣያ ውስጥ ወረቀት እየጣሉ ሲያቃጥሉ በመታየቱ ነው ተብሏል።

ጊቢው ውስጥ ወረቀት እየተቃጠለ መሆኑ ለሂውስተን ፖሊስ ተነግሮ፤ የጸጥታ ኃይሎች ወደ ቆንስላው ቢያመሩም፤ ወደ ውስጥ ለመግባት ፍቃድ እንዳላገኙ ተናግረዋል።

ይህን ተከትሎ ቻይና ቆንስላውን እንድትዘጋ 72 ሰዓታት ተሰጥቷት ነበር። ይህም የአሜሪካን አዕምሯዊ ንብረትና የአሜሪካውያንን ግላዊ መረጃ ለመጠበቅ ነው ተብሏል።

ከክስተቱ በኋላ ማይክ ፖምፔዮ “የቻይና ኮምኒስት ፓርቲ ምን እንደሚያደርግ እናውቃለን፤ አሜሪካውያንን፣ ብሔራዊ ደኅንነታችንን እና ምጣኔ ሀብታችንን ለመጠበቅ እርምጃ እንወስዳል” ብለዋል።