እንግሊዝ ከሆንግ ኮንግ ጉዳይ እጇን እንድትሰበስብ ቻይና አስጠነቀቀች

ዩናይትድ ኪንግደም ከሆንግ ኮንግ ጉዳይ 'እጇን የማታነሳ' ከሆነ 'መዘዙን ልትቀበል እንደምትችል' ቻይና አስጠነቀቀች።

ዕለተ ሰኞ ዩናይትድ ኪንግደም፤ ቻይና አዲስ ያወጣችውን ሕግ በመቃወም ከሆንግ ኮንግ ጋር የነበራትን ወንጀሎችን የመለዋወጥ ስምምነት ሰርዛለች።

ለዚህ የዩናይትድ ኪንግደም ድርጊት ምላሽ ሎንዶን የሚገኙት የቻይናው አምባሳደር ዩኬ በቻይና የውስጥ ጉዳይ 'እጇን እየሰደደች' ነው ሲሉ ወርፈዋል።

አምባሳደር ሊዩ ዢያዎሚንግ 'ቻይና በዩናይትድ ኪንግደም ጉዳይ ጣልቃ ገብታ አታውቅም። ዩኬም ይህን ልታደርግ ይገባል' ብለዋል።

በያዝነው ወር መባቻ የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን 'ሶስት ሚሊዮን የሆንግ ኮንግ ነዋሪዎች ዩናይት ኪንግደም መጥተው መኖር የሚችሉትን ዕድል እናመቻቻለን፤ የብሪታኒያ ዜግነትም ማመልከት ይችላሉ' ብለው ነበር።

በሌላ በኩል ዩኬ የቻይናው ሁዋዌ ቴክኖሎጂ የሃገሪቱን 5ጂ ኢንተርኔት ዝርጋታ እንዳያከናውን ማድረጓ አይዘነጋም።

ቻይና፤ ሆንግ ኮንግ ውስጥ ወንጀል የፈፀሙ ሰዎች ወደ ቤይዢንግ ተወስደው ጉዳያቸው ይታያል የሚል ሕግ ማፅደቋን ተከትሎ ነው ዩኬ ውሳኔውን ያስተላለፈችው።

ተቺዎች አዲሱ የቻይና ሕግ ለዲሞክራሲ የሚጮሁ የሆንግ ኮንግ ክልል ነዋሪዎችን ለዕድሜ ልክ እሥር ሊያጋልጥ ይችላል ሲሉ ይወቅሳሉ።

የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፓምፔዮ ሎንዶን ናቸው። ሚኒስትሩ ከጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጋር ስለ ቻይና እና ኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የብሪታኒያ የቀድሞ ቅኝ ግዛት የሆነችው ሆንግ ኮንግ የወንጀሎችና እሥረኞች ልውውጥ ውል ከዩኬ ጋር የገባችው ከሃምሳ ዓመታት በፊት ነው።

የዩኬ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶሚኒክ ራብ ከሆንግ ኮንግ ጋር የተገባው ስምምነቱ መቋረጡን ይፋ ያደረጉት ሰኞ ዕለት ነው። 'አዲሱ የቻይና ሕግ እንዴት ሊተገበር እንደሚችል እርግጥ ያለሆኑ ጉዳዮች ስላሉ ነው ስምምነቱን ያቋረጥነው' ብለዋል።

በውሳኔው መሠረት ዩኬ ያለ ነገር ግን ሆንግ ኮንግ ውስጥ ወንጀል በመፈፀም የተጠረጠረ ሰው ተላልፎ አይሰጥም ማለት ነው።

አምባሳደር ሊዩ በትዊተር ሰሌዳቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት ዩኬ ዓለም አቀፍ ሕግጋትን የሚጋፋ ተግባር ፈፅማለች ሲሉ ወቅሰዋል።

በእንግሊዝ የቻይና ኤምባሲ ድረ-ገፅ ላይ የታተመ መግለጫ፡ "ቻይና፤ ዩኬ በሆንግ ኮንግ ጉዳይ ጣልቃ ከመግባት ትቆጠብ። ጉዳዩ የቻይና ነው" ሲል ያትታል።

"ዩናይት ኪንግደም የተሳሳተ መንገድ ከመረጠች መዘዙን ለመቀበል ልትዘጋጅ ይገባል።"

ሚኒስትር ራብ ባለፈው እሁድ ቻይና የዊገር ሙስሊሞች ላይ በደል እየፈፀመች ነው ሲሉ መውቀሳቸው አይዘነጋም። ነገር ግን አምባሳደር ሊዩ የማጎሪያ ካምፖች አሉ እየተባለ የሚወራው 'ሃሰተኛ ዜና' ነው አስተባብለዋል።

ከዩኬ በተጨማሪ አሜሪካም ሁዋዌ የተሰኘው ቴክኖሎጂ ለብሔራዊ ደህንነት ስጋት ነው ትላለች። ኩባንያው ግን ክሶቹን አስተባብሏል።