የአያ ሶፍያን ወደ መስጂድነት መቀየርን በመቃወም የአለም አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ አቤቱታ አስገባ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የአለም የአብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ ቱርክ ታሪካዊዋን አያ ሶፍያ ሙዚየም ወደ መስጂድ ለመቀየር መወሰኑን ተከትሎ ለፕሬዚዳንት ጣይብ ኤርዶጋንን ይህንን ውሳኔያቸውን እንዲቀለብሱ አቤቱታ አስገብቷል።
ከሶስት መቶ አባላት በላይ ያሉት ይህ ጉባኤ ለፕሬዚዳንቱ በፃፈው ደብዳቤ ይህ ውሳኔ "መከፋፈልን የሚፈጥር ነው" ብሏል።
በጄኔቫ መቀመጫውን ያደረገው ይህ ጉባኤ ከአምስት መቶ ሚሊዮን በላይ ክርስቲያኖችን በመወከል ደብዳቤውን እንደፃፈ አሳውቋል።
ውሳኔው ያልተጠበቀና "አሳዛኝም ነው" ብሏል። "አያ ሶፍያን ወደ መስጂድነት በመቀር የቱርክ አዎንታዊ መለያ የነበረውን ተቀባይነትና መቻቻል በመቀልበስ ወደ መከፋፋልና ማግለል ለውጣችሁታል" በማለትም ደብዳቤው አትቷል
ደብዳቤው አክሎም ውሳኔው ጥርጣሬዎችንና አለመተማመኖችን እንደሚያሰፍን ገልፆ በተለያዩ እምነቶች መካከል የሚደረጉ መተባበሮችና ንግግሮችንም የሚያደፈርስ ነው ብሏል። ከዚህ ቀደም የነበሩ ጥርጣሬዎችንና መከፋፈሎችንም ለማስቀረት ውሳኔው እንዲቀለበስ ደብዳቤው ጠይቋል።
ከጎርጎሳውያኑ 1934 ወደ ሙዝየምነት የተቀየረው ይህ ታሪካዊ ቦታ በዩኔስኮ የአለም አቀፍ ቅርስነትም ተመዝግቧል።
ፕሬዚዳንቱ ይህንን ውሳኔያቸውን ያሳወቁት ባለፈው አርብ ሲሆን ፍርድ ቤት ቦታው ሙዚየምነቱ ይቅር የሚል ውሳኔም መድረሱን ተከትሎ ነው።
አያ ሶፍያ ከአንድ ሺ አምስት መቶ አመት በፊት የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ካቴድራል ነበረች። ስፍራው በጎርጎሳውያኑ 1453 ወደ መስጂድነትም የተቀየረው በኦቶማን መያዟን ተከትሎ ነው።
ሃይማኖትና መንግሥት የተለያየ ነው የሚሉት የዘመናዊዋ ቱርክ መስራች ሙስጠፋ ከማል አታቱርክ ወደ ስልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ ቦታው ወደ ሙዚየም እንዲቀየር ተወሰነ።
ይህንንም ተከትሎ ማንኛውም የአምልኮ አገልግሎቶች እንዲታገዱ ትእዛዝ ተላልፎ የነበረ ቢሆንም በርካታ የእስልምና እምነት ተከታዮች አምልኮ እንዲፈቀድም ዘመቻ ሲያካሂዱ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ህንፃው ከቤተክርሰቲያን ወደ መስጂድነት የቀየሩት የኦቶማን ሱልጣን መህመድ የግል ንብረት እንደሆነ በመከራከር መስጂድ መሆን ይችላል በማለትም ፕሬዚዳንት ኤርዶጋንን ጨምሮ በርካቶች ሲከራከሩ ነበር።
ይኼም ሁኔታ የሃይማኖትን ጣልቃ ገብነት በማይፈልጉ ቱርካውያን ዘንድ ቅሬታን ፈጥሯል።
ፕሬዚዳንቱ በበኩላቸው አገራቸው ሉዓላዊ መብቷን በመጠቀም ሙዚየሙን ወደ መስጂድነት እንደቀየረችው አፅንኦት ሰጥተው የመጀመሪያውም የአምልኮ ስርአት ከሁለት ሳምንታት በኋላ ይሆናል ተብሏል።
"እንደ ሁሉም መስጂዶች አያ ሶፍያም ለዜጎችና ለሌላ አገር ዜጎች እንዲሁም ለእስልምና እምነት ተከታይ ለሆኑም ሆነ ላልሆኑት ክፍት ይሆናል" ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት በቱርክ ለአምልኮ የሚሆኑ 435 አብያተ ክርስቲያናትና ምኩራቦች አሉ ብለዋል።
የፕሬዚዳንቱ ውሳኔ ግን በጉባኤው ብቻ ሳይሆን በዩኔስኮም ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም፤ "ሃዘን ተሰምቶናል" ብሏል ከዩኔስኮ የወጣው መግለጫ።
የምስራቅ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ኃላፊም ውሳኔውን አውግዘውታል።
በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ያሏት ግሪክም "የሰለጠነው አለምን የሚተነኩስ" ብላዋለች።
በአለም ከፍተኛ ቁጥር የኦርቶዶክስ ምዕመናን ያሏት ሩሲያም የቱርክ ፍርድ ቤት የሃጊያ ሶፍያ ታሪካዊ ሁኔታ ባለማጤኑ አሳዛኝ መሆኑን ገልፃለች።
ከዚህም በተጨማሪ የሃይማኖትን ጣልቃ ገብነት በማይፈልጉ ሚሊዮኖች ቱርካውያንም ውሳኔውን አውግዘውታል።












