ሰዎች ቤት ተቀምጠው ሳለ ሲሰራ የከረመው ሮቦት

የሮቦት እጅ በኮምፒውተር ኪቦርድ ላይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በሊቨርፑል ዩኒቨርሲቲ ያሉ ሳይንቲስቶች የሰው ልጅ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ቤቱ ተቀምጦ ሳለ ሥራ ሲሰራ የነበረ ሮቦትን ለሕዝብ ይፋ አድርገዋል።

100 ሺህ ፓውንድ የሚያወጣው ይህ ሮቦት በተጫነለት ፕሮግራም የሚሰራ ነው ተብሎለታል።

"በፕሮግራም የሚሰራ ስለሆነ ቤት ቁጭ ብዬ ሥራ ላዘው እችላለሁ" ይላሉ ከተመራማሪዎቹ አንዱ የሆኑት ቤንጃሚን በርገር።

ሳይንቲስቶቹ እንደሚሉት ሮቦቱ የሰው ልጅ የሚሰራውን አንድ ሥራ በአንድ ሺህ እጥፍ ፍጥነት ማገባደድ ይችላል።

ሮያል ሶሳይቲ ኦፎ ኬሚስትሪ የተሰኘው ተቋም ያወጣው አንድ ዘገባ እንደሚጠቁመው ሮቦት ተጠቅሞ ድህረ-ኮሮናቫይረስ ጥናት ለማካሄድ እየተሞከረ ነው።

ጥናቱ ሰው ሰራሽ ልህቀትና [አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ] የላቁ ኮምፒውተሮችን በመጠቀም ሳይንቲስቶች ቤታቸው ሆነው ሥራቸውን እንዲተገብሩ ከማስቻሉም በላይ ሌሎች ዓለም አቀፍ ችግሮችንም ሊፈታ ይችላል እየተባለ ነው።

የሮቦት ሳይንቲስቶች በአሁኑ ወቅት የተለያዩ ጥናቶችን በማካሄድ ላይ ናቸው። ከእነዚህም አንዱ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን መግታት ነው።

ፕሮፌሰር አንዲ ኩፐር ሮቦቶችን ወደ ቤተ ሙከራቸው አስገብተው የተለያዩ ምርምሮች እያደረጉ ነው።

"ኮቪድ-19፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና ሌሎችም ዓለም አቀፍ ትብብር የሚሹ የተለያዩ ችግሮች አሉ። የእኛ ዓላማ በማዕከላዊ አእምሮ የተገናኙ ሮቦቶች በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች አሰራጭቶ ምርምር ማድረግ ነው። እርግጥ ነው እስካሁን ያንን አላደረግንም፤ ነገር ግን ማድረጋችን አይቀርም።"

ሳይንቲስቶቹ ከቤተ-ሙከራቸው ራቅ ብለው ምርመራ ለማድረግ በተገደዱበት በዚህ ወቅት ሮቦቶች ምርጥ መላ ሆነዋል።

"ሮቦት አይደክመው፣ አይሰለቸው። ከንጋት እስከ ንጋት ይሰራል፤ በዚያ ላይ ለበዓል እረፍት ልውጣ አይል" ሲሉ ዶ/ር በርገር ቀልድ ቢጤ ጣል አድርገዋል።

ቀልዱን ለጊዜው ረስተነው ይላሉ ሳይኒስቱ ሮቦቱ ለሰው ልጅ በርካታ ጊዜ የሚወስድበትን ሥራ በፍጥነት እያጠናቀቀ ነው። "ይህ ደግሞ እኔ ወደ ፈጠራ ሥራዬ ትኩረቴን እንዳደርግ ረድቶኛል" ይላሉ።

ሕዋ ላይ ምርምር እንዲያደርጉ እንደተፈጠሩ ሮቦቶች ሁሉ ይህኛው ሮቦት ፈተናን ተቋቁሞ ሥራውን እንዲከውን እየሠለጠነ ነው።

የሮያል ሶሳይቲ ኦፍ ኬሚስትሪ ኃላፊ የሆኑት ዳዬርድሬ ብላክ የዩናይትድ ኪንግደም የሳይንስ ዘርፍ ሮቦቶች ላይ መዋዕለ ነዋይ ሊያፈስ ይገባል ብለው ያምናሉ።

ነገር ግን አንድ አንገብጋቢ ጥያቄ አሁንም ምላሽ አላገኘም። እንዲህ ከሆነ ሮቦቶች የሰውን ልጅ ሥራ እየወሰደ ነው ማለት?

ዶክተር ብላክ "ኧረ በጭራሽ" ይላሉ። "ሳይንስ ምንም ጊዜ ቢሆን የሰው ልጅን እርዳታ ይሻል" በማለት የሚያሰጋ ነገር እንደሌለ ያሰምሩበታል።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, ሮቦት ገበሬዎች የሰዎችን ስራ ሊነጥቁ ነው።