ጥቁር ሞትን ዳግም ሊቀሰቅስ የሚችለው ወረርሽኝ በቻይና ታየ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቻይና ባለስልጣናት ራስ ገዝ በሆነችው ኢነር ሞንጎሊያ ግዛት ውስጥ ቡቦኒክ የተሰኘ በሽታ በመከሰቱ ቅድመ ጥንቃቄ መውሰድ ጀመሩ።
እንደ ቻይና መገናኛ ብዙሃን ዘገባ ከዚህ በሽታ ጋር በተያያዘ በአንዲት የገጠር መንደር ውስጥ የሚኖር እረኛ በለይቶ ማቆያ የገባ ሲሆን አሁን በተሻለ ጤንንት ላይ ይገኛል ተብሏል።
ባለስልጣናቱ ደረጃ 3 ያሉትን ማስጠንቀቂያ ያወጡ ሲሆን ይህም በሽታው ገና ዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንዳለ እንደሚያሳይ ተገልጿል።
የቡቦኒክ ወረርሽኝ በባክቴሪያ የሚከሰት ሲሆን በቀላሉ በአንቲባዮቲክ ማከም እንደሚቻል ነገር ግን ታማሚው ሕክምና ካላገኘ ግን በሽታው ሊገድል እንደሚችል የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ።
በቻይና የመጀመሪያው የቡቦኒክ ወረርሽኝ የተመዘገበው ቅዳሜ ዕለት ሲሆን ይህም በኡራድ ሚድል ባነር ሆስፒታል በባያኑር ከተማ ውስጥ ነው።
እስካሁን ድረስ ታካሚው እንዴትና ለምን በበሽታው ሊያዝ እንደቻለ ፍንጭ አልተገኘም ተብሏል።
ባለስልጣናቱ ያወጡት ደረጃ 3 ማስጠንቀቂያ እንስሳት ወረርሽኙን ሊሸከሙ ስለሚችሉ ማደንም ሆነ መመገብ የሚከለክል ሲሆን እንዲሁም በተመሳሳይ በሽታ መያዙን የሚጠረጥሩትን ሰው እንዲያሳውቁ ይጠይቃል።
እስካሁን በዓለም ላይ በቡቦኒክ ወረርሽኝ የተያዙ ሰዎች በተለያየ ጊዜ ተገኝተዋል።
በ2017 ማዳጋስካር ውስጥ 300 ያህል ሰዎች በበሽታው ተይዘው ነበር።
ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ ሁለት ሰዎች በሞንጎሊያ በዚህ ወረርሽኝ የተነሳ ሲሞቱ የማርሞት (የአይጥ ጥዝርያ) ጥሬ ሥጋን በልተው መያዛቸው ተገልጿል።
የዓለም ጤና ድርጅት በሞንጎሊያ ዋና ከተማ ኡላንባታር ለቢቢሲ እንደተናገረው፤ በአካባቢው የማርሞት ጥሬ ሥጋና ኩላሊት ለመልካም ጤንነት ፍቱን ነው ተብሎ ይታመናል።
የአይጥ ዝርያ የሆነችው ማርሞት ባክቴሪያውን ተሸካሚ ብቻ ሳትሆን በአገሪቱ የተከሰቱ ወረርሽኞችም መነሻ እንደሆነች ይታመናል።
ቡቦኒክ ወረርሽኝ የሊምፍ ኖዶች (በአንገትና በብብት አካባቢ የሚገኙ) እብጠትን የሚያስከትል ሲሆን በመጀመሪያዎቹ ሳምንታት በቀላሉ ምልክቶቹን ለመለየት አስቸጋሪ ነው ተብሏል።
የቡቦኒክ ወርረሽኝ ከዚህ ቀደም ጥቁር ሞት እየተባለ የሚታወቀው ወረርሽኝ ሲሆን በዚህም ወረርሽኝ የተነሳ በ14ኛው ክፍለ ዘመን 50 ሚሊዮን ሰዎች በመላው ዓለም ላይ መሞታቸው ይጠቀሳል።













