"የቻይናና የአሜሪካ ቀዝቃዛው ጦርነት ከኮሮናቫይረስ በላይ ለዓለም ያሰጋል"

ሊቅ ጄፍሪ ሳክስ

የፎቶው ባለመብት, MICHAEL KOVAC

በመጪዎቹ ዓመታት በአሜሪካና በቻይና መካከል ሊከሰት የሚችለው ቀዝቃዛ ጦርነት ዓለምን ከኮሮናቫይረስ በላይ ሊያስጨንቅ እንደሚገባ ዕውቁ የምጣኔ ሀብት ሊቅ ጄፍሪ ሳክስ ተናገሩ።

የኮሎምቢያው ዩኒቨርስቲ ዕውቅ ፕሮፌሰር ጄፍ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ዓለም ወደ አንዳች መደነቃቀፍ እያመራች ነው፤ መሪ አልባም ሆናለች ብለዋል።

እንዲሁም የዓለም ሁኔታ መልክ ባልያዘበት ሁኔታ በሁለቱ የዓለም ኃያላን መካከል ያለው ቁርሾና ቅራኔ እየባሰ ከሄደ ሁኔታዎችን ያባብሳል፤ ጦሱም ለተቀረው ዓለም ይተርፋል ብለዋል።

እኚህ ፕሮፌሰር ለዚህ ሁሉ ተጠያቂዋ አሜሪካና አመራሯ ነው ብለዋል።

አሁን ያለው የአሜሪካ አመራር ከትብብር ይልቅ ክፍፍልን የሚያፋፍም ነው ሲሉም ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"አመራሩ አዲስ ቀዝቃዛ ጦርነት ከቻይና ጋር ለመፍጠር እየሞከረ ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ ዓለምን ዳግም ወደ ሰላም ለመመለስ በጣም ይቸገራል" ብለዋል ፕሮፌሰሩ።

የፕሮፌሰር ጄፍሪ ሳክስ አስተያየት የመጣው ሰሞኑን ቻይናና አሜሪካ ከምጣኔ ሀብት ጦርነት ጋር ብቻም ሳይሆን ፖለቲካዊ መቆራቆዝ ውስጥ እየገቡ ስለመሆኑ ምልክቶች መታየታቸውን ተከትሎ ነው።

በያዝነው ሳምንት ለምሳሌ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ በቻይና ባለሥልጣናት ላይ ማዕቀብ የሚጥለው ሰነድ ላይ ይፈርማሉ ተብሏል።

ማዕቀቡን የሚጥሉት በዢንጂያንግ ግዛት የቻይና ሙስሊሞችን ለርዕዮተ ዓለም ጥምቀት ማጎርያ ውስጥ መከተታቸውን ተከትሎ ነው።

ያም ሆኖ የዶናልድ ትራምፕ የቀድሞው የደኅንነት አማካሪ ሰሞኑን ለአንባቢዎች ያደርሱታል በተባለው አዲስ መጽሐፋቸው እንደጠቀሱት፤ ፕሬዝዳንቱ ቻይና ይህንን የሙስሊሞች ማጎርያ እንድትገነባ አበረታተው ነበር።

ዶናልድ ትራምፕ ከሰሞኑ ከዎልስትሪት ጆርናል ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ቻይና ኮሮናቫይረስን ለዓለም ያቀበለችውና ብሎም ያሰራጨችው ሆን ብላ የአሜሪካንን ምጣኔ ሀብት ለማንኮታኮት ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የቻይናና የአሜሪካንን የኢኮኖሚ ጦርነት ካመላከቱ ነገሮች አንዱ አሜሪካ በቻይናው ግዙፍ የቴሌኮም ኩባንያ ሁዋዌ ላይ የጣለችው እቀባ ነው። አሜሪካ እንደምትለው ሁዋዌ የደንበኞችን መረጃ ለመሰለል የተቋቋመ ነው። ቻይና ይህንን ክስ ታስተባብላለች።

የአሜሪካ ባንዲራና የሁዋዌ አርማ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, አሜሪካ በቻይናው ተቋም ሁዋዌ ላይ ጥርጣሬ አላት

የቀድሞው የዶናልድ ትራምፕ ከፍተኛ የደኅንነት አማካሪ ጆን ቦልተን አዲስ በጻፉት መጽሐፍ እንዳጋለጡት ከሆነ ዶናልድ ትራምፕ ህዋዌ ላይ እቀባ ያደረጉት በድጋሚ የመመረጥ ዕድላቸውን ለማስፋት ብቻ ነው።

ፕሮፌሰር ጄፍሪ ሳክስም በዚህ የቦልተን ሐሳብ ይስማማሉ። ሁዋዌን ትራምፕ ያገዱት የምርም የደኅንነት ጉዳይ አሳስቧቸው ሊሆን አይችልም።

"አሜሪካ በ5ጂ የሞባይል ቴክኖሎጂ ተቀድማለች። ሁዋዌ ደግሞ የዓለምን የገበያ ድርሻ ተቀራምቶታል፤ ይህ ነው አሜሪካንን የረበሻት" ይላሉ።

ከቻይና ጋር ፍጥጫ ላይ ያለችው አገር አሜሪካ ብቻ አይደለችም። ቻይና ባለፈው ሳምንት ከሕንድ ጋር የድንበር ግጭት ውስጥ ገብታ 20 የሕንድ ወታደሮችን መገደላቸው አይዘነጋም።

ይህ በእንዲህ እናዳለ ቻይና በፓኪስታን፣ በምያንማር፣ በሲሪሊንካና በኔፓል በርካታ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን እያገዘች ነው። እነዚህ አገራት ደግሞ የሕንድ ጎረቤቶች ናቸው።

ሕንድ ቻይና የአካባቢው ተጽእኖ ፈጣሪ አገር የመሆኗን ጉዳይ ማስቆም ትፈልጋለች።

ፕሮፌሰር ሳክስ እንደሚያምኑት ቻይና በአካባቢው አገራት ላይ የትብብር መንፈስ ካሳየች ነገሮች የተሻሉ ይሆናሉ።

ቻይና እድሏ ያለው በእጇ ነው። ቻይና ተባባሪ ከሆነች፣ በዲፕሎማሲ ችግሮችን ለመፍታት ከፈለገችና የትብብር መንፈስ ካሳየች ጉልበት ያላት አገር ስለሆነች ብዙ ነገር መቀየር ትችላለች፤ የእሲያ አህጉርም የተሻለ መጻኢ እድል ይኖረዋል።