የኢትዮጵያ 10ኛው ክልል ከደቡብ ክልል የስልጣን ርክክብ አካሄደ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ውስጥ አንድ ዞን በመሆን ለሦሰት አስርት ዓመታት ያህል የቆየው የሲዳማ ዞን የአገሪቱ አስረኛ ክልል ሆነ።
የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት ዛሬ ማካሄድ በጀመረው አስቸኳይ ጉባኤው የሲዳማ ዞን በሕዝበ ውሳኔ በክልል እንዲደራጅ በተገኘው ውጤት መሰረት የሥልጣን ርክክብ ርክክብ ተፈጽሟል።
በዚህም መሰረት የደቡብ ክልል እና አዲሱ የሲዳማ ክልል በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ምክር ቤት አባላት ፊት የዞኑን ስልጣን በማስረከብ ዞኑ ክልል መሆኑ ይፋ ሆኗል።
የሲዳማ ሕዝብ በኅዳር ወር (ህዳር 10/2012 ዓ.ም) ባካሄደው ሕዝበ ውሳኔ ላይ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ድምጽ ሰጠ ሲሆን፤ ዞኑ ክልል እንዲሆን የሚያስችለውን ከፍተኛ ድምጽ በማግኘቱ ነው እዚህ ውሳኔ ላይ የተደረሰው።
የሲዳማ ሕዝብ በከፍተኛ ድምጽ ራሱን ችሎ ክልል እንዲሆን መወሰኑን የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ያሳወቀው ደግሞ ኅዳር 13/2012 ነበር።
የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ርስቱ ይርዳው የሲዳማ ክልል ራሱን ችሎ በመውጣቱ በሌሎች ሕዝቦች ላይ የሚፈጥረው ተጽዕኖ እንደማይኖር መናገራቸው ፋና ዘግቧል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አሁን ያለው ፌደራላዊ አወቃቀር ተግባራዊ ከሆነ በኋላ የነበሩ አምስት ክልሎችን በማዋሃድ የተፈጠረ ከ50 በላይ ብሔርና ብሔረሰቦች የሚገኙበት ክልል ነው።
የሲዳማ ዞን ራሱን የቻለ ክልል ለመሆን ለዓመታት ጥያቄ ሲያቀርብ ቆይቶ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ አስተዳደር ከመጣ በኋላ ጥያቄው ተጠናክሮ በሕዝበ ውሳኔ እልባት አግኝቷል።
ከሲዳማ በተጨማሪ በደቡብ ክልል ውስጥ ያሉ ከአስር የሚበልጡ ዞኖች የእራሳቸው ክልል እንዲኖራቸው ጥያቄ ማቅረባቸው በተደጋጋሚ ሲገለጽ ነበር።
ማክሰኞ ሰኔ 2/2012 ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ከደቡብ ክልል የዞን እና የልዩ ወረዳ አስተዳዳሪዎች ጋር ተገናኝተው ከተነጋገሩ በኋላ የሲዳማ ዞንን ጨምሮ የደቡብ ክልልን በአራት የሚከፍል አዲስ አወቃቀር ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲተላለፍ ከስምምነት ላይ መደረሱ ተሰምቷል።















