በኢንዶኔዢያዋ የውሃ ጉድጓድ ውስጥ ወድቆ ስድስት ቀናት የቆየው ኢንግሊዛዊ በህይወት ተገኘ

የፎቶው ባለመብት, BASARNAS BALI
በኢንዶኔዢያዋ ባሊ ደሴት የውሃ ጉድጓድ ውስጥ ወድቆ ለስድስት ቀናት የቆየው እንግሊዛዊ በስተመጨረሻ ሕይወቱን ማትረፍ ተችሏል።
የ29 ዓመቱ ጄኮብ ሮበርትስ በፔካቱ መንደር ውሻ ሲያሯሩጠው ለማምለጥ ሲሞክር ነው አራት ሜትር በሚጠልቀው ጉድጓድ ውስጥ የወደቀው።
ከአደጋው በኋላ እግሩ እንደተሰበረ የአካባቢው ባለስልጣናት ገልጸዋል። ምንም እንኳን ጉድጓዱ ውሃ ባይኖርበትም እግሩ በመሰበሩ ምክንያት መውጣት ሳይችል ቆይቷል።
በአካባቢው የነበሩ የአይን እማኞች እንደገለጹት በጉድጓዱ ውስጥ ትንሽ ውሃ በመኖሩ ለስድስቱ ቀናት የሚጠጣውን ማግኘት ችሏል። ጄኮብ ሮበርትስ ለስድስት ቀናት ያለመታከት የድረሱልኝ ጥሪውን ሲያሰማ ነበር። በመጨረሻም አንድ የአካባቢው ነዋሪ ድምጹን በመስማቱ ሕይወቱ ልትተርፍ ችላለች።
እምብዛም ሰዎች በማይኖሩበት አካባቢ በሚገኘው የውሃ ጉድጓድ አቅራቢያ ከብቶቹን ሲጠብቅ የነበረው ግለሰብ ሁኔታውን ከተመለከተ በኋላ ወዲያው የአካባቢው ኃላፊዎችን ጠርቷል።
ጃኮብ በግለሰቡ የተገኘው ባሳለፍነው ቅዳሜ ሲሆን ወዲያውኑ ከጉድጓዱ ወጥቶ ህክምና እንዲያገኝ ተደርጓል።
ደሴቲቱ ውስጥ የምትገኘው የፔካቱ መንደር እንደ ጄኮብ ያሉ በርካታ ጎብኚዎች የሚያዘወትሯት ሲሆን እንዲህ አይነት አደጋ እምብዛም የተለመደ አይደለም ተብሏል።








