ፓኪስታናዊው ህንድ'በሰላይነት' የያዘቻት 'እርግቤን' ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይመልሱልኝ እያለ ነው

ከሰሞኑ ህንድ በሰላይነት የያዘቻት እርግብ እንድትለቀቅ ባለቤት ነኝ ያለው ፓኪስታናዊ የሃገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲን ጠይቋል።

በህንድ አራት ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኝ የድንበር ከተማ ላይ ነዋሪ የሆነው ግለሰብ እርግቧን የለቀቃት የኢድ አልፈጥርን በዓል ለማክበር እንደሆነ አሳውቋል።

የህንድ ፖሊስ በበኩሉ እርግቧ በእግሯ ላይ ቀለበት እንዳላትና የተለያዩ ሚስጥራዊ ኮዶችን (የይለፍ ቃል) የያዘች መሆኗን ገልፀው፤ የይለፍ ቃሉ (ኮዱ) ምን እንደሆነም እየመረመሩ እንደሆነ አሳውቀዋል።

ግለሰቡ በበኩሉ የይለፍ ቃል የተባለው የስልክ ቁጥር መሆኑን አስታውቋል። የፓኪስታኑ ዳውን ጋዜጣ በበኩሉ የእርግቧ ባለቤት ስሙ ሃቢቡላህ መሆኑንና በርካታ እርግቦችም እንዳሉት ዘግቧል።

እርግቦቹ የሰላም ምልክት መሆናቸውንና ህንድ "ይህችን ምንም ያላጠፋች ነፃ እርግብ ጥቃት እንዳታደርስባት" መናገሩን ጋዜጣው ሃቢቡላህን ዋቢ አደርጎ ዘግቧል።

እርግቧ የተያዘች ህንድና ፓኪስታን ይገባኛል በሚሏት የካሽሚር ግዛት ሲሆን፤ በህንድ በኩል በምትደዳደረው ግዛትም እርግቧ መግባቷን ተከትሎ የአካባቢው ማህበረሰብ ለፖሊስ አሳልፈው ሰጥተዋታል።

ከፓኪስታን የበረረች እርግብ በህንድ ባለስልጣናት 'በሰላይነት' ስትፈረጅ የመጀመሪያዋ አይደለም።

በጎርጎሳውያኑ 2015 አንዲት ነጭ እርግብ በሁለቱ ሃገራት ድንበር በኩል ስታንዣብብ በአስራ አራት አመት ታዳጊ ጠቋሚነት ታስራ ነበር።

እንዲሁ በጎርጎሳውያኑ 2016ም የህንዱን ጠቅላይ ሚኒስትር ማስፈራሪያ ወረቀት ተገኘባት የተባለች ሌላ እርግብ በቁጥጥር ስር ውላለች።

ሁለቱ ሃገራት ለዘመናት ተፋጠው የሚገኙ ሲሆን፤ በጎርጎሳውያኑ 1971ም ከፍተኛ ጦርነት ውስጥ ገብተው ነበር። በተለይም በካሽሚር ግዛት ይገባኛል የተነሳ ሁለቱ ሃገራት ስምምነት ላይ መድረስ አልቻሉም።