ፈረንሳይ በየዓመቱ አንድ ሚሊዮን የኤሌክትሪክ መኪና ልታመርት ነው

የፎቶው ባለመብት, AFP /GETTY IMAGES
የኮሮናቫይረስ እስከናካቴው በኪሳራ እንዳያጠፋቸው ሲፈራላቸው የነበሩት የፈረንሳይ የመኪና አምራቾች በክፉ ጊዜ መንግሥት ደርሶላቸዋል።
በድምሩ 8 ቢሊዮን ዩሮ ለድጎማ የመደበው የማክሮን መንግሥት 1 ቢሊዮኑ ለመኪና አምራቾች በቀጥታ የሚሰጥ ሲሆን ቀሪው 7 ቢሊዮን ዩሮ ደግሞ መኪና ሸማቾች የኤሌክትሪክ መኪና እንዲገዙ ማበረታቻ ይሆናል።
ይህ የድጎማ ምክረ ሐሳብ የቀረበው የፈረንሳይ የመኪና አምራቾች በርካታ ሠራተኞችን ከሥራ እያባረሩ ባለበት ሰዓት ነው። ሬኖ በሚቀጥሉት 4 ዓመታት ውስጥ 5ሺ ሠራተኞችን ለመቀነስ እቅድ ይዞ ነበር።
ድጎማውን ተከትሎ ሁለቱ የፈረንሳይ መኪና አምራቾች ሬኖ እና ፒኤስኤ ምርታቸውን በፈረንሳይ መሬት ላይ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።
ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ፈረንሳይን በዓለም ኤሌክትሪክ መኪና ቁጥር አንድ አምራች እንድትሆን ይፈልጋሉ።
"በሚቀጥሉት 5 ዓመታት ቢያንስ በየዓመቱ 1 ሚሊዮን የኤሌክትሪክና የነዳጅ-ኤሌክትሪክ ቅይጥ መኪኖችን በማምረት ለአየር ንብረት ለውጥ የገባነውን ቃል እናሳካለን" ብለዋል ማክሮን።
ኢማኔኤል ማክሮን የአገሬ አምራቾች የፈረንሳይን መኪና ከፈረንሳይ ምድር ውጭ እንድታመርቱ አልፈልግም ሲሉ የአገር ውስጥ የሥራ ዕድል እንዲስፋፋ ያላቸውን ምኞት ገልጠዋል።
በፈረንሳይ በኮቪድ-19 ምክንያት ግማሽ ሚሊዮን መኪናዎች በየመደብሩ ገዢ አጥተው ቁጭ ብለዋል። ዜጎች ታዲያ የድሮ መኪናቸውን ትተው አየር በካይ ያልሆኑ የኤሌክትሪክ መኪናዎችን እንዲገዙ የ3 ሺህ ዩሮ ድጎማ ይደረግላቸዋል ተብሏል።
"ዜጎቼ ንጹህ መኪና እንዲገዙ ነው የምፈልገው፤ አየር በካይ መኪና በፈረንሳይ ሊነዳ አይገባም። ዜጎቼ መኪናዎቹን እንዲገዙ የምፈልገው ወደፊት አይደለም፤ ዛሬ ነው" ብለዋል ማክሮን።
በፈረንሳይ ወረርሽኙን ተከትሎ ከፍተኛ የመኪና ንግድ መቀዛቀዝ የተከሰተ ሲሆን አሁን ላይ ግማሽ ሚሊዮን መኪናዎች ገዢ ያለህ እያሉ ነው።
ማክሮን በዚህ ግዙፍ የመኪና ድጎማ እቅዳቸው ሦስት ነገር ማሳካት ይፈልጋሉ። አንደኛው ፈረንሳይ ብዙ መኪናዎች አምራች እንድትሆን ነው፤ ሁለተኛው መኪናዎቹ የሚመረቱት በቻይና ሳይሆን በአገራቸው እንዲሆን ነው፤ ሦስተኛው የሚመረቱት መኪናዎች ከአየር ብክለት የጸዱ እንዲሆኑ ነው።
በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንዲሉ የማክሮን ሐሳብ አሁን በክፉው ጊዜ ከፍተኛ ድጎማ ለዜጎች ቢደረግ፣ አምራቾችም ሥራቸውን እንዲያቀላጥፉ ቢበረታቱ ያንቀላፋውን የመኪና ገበያ በከፍተኛ ሁኔታ አነቃቅቶ በዚያውም በካይ መኪናዎች ከመንገድ ውጭ ይሆናሉ የሚል ነው።
በመጪዎቹ ጥቂት ዓመታት የኤሌክትሪክ መኪናዎች በእጥፍ እንደሚያድጉ በመገመቱ ፈረንሳይ የመኪና ባትሪ ቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያዎችን ቁጥር ወደ 100 ሺህ ለማድረስ እየሰራች ነው።












