የሌሴቶ ጠቅላይ ሚንስት ቶማስ ታባኔ ከሥልጣን ለቀቁ

ቶማስ ታባኔ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, የ80 ዓመቱ ቶማስ ታባኔ ረዥም ዓመታት ስልጣናቸው ላይ ከቆዩ አፍሪካ መሪዎች መካከል አንዱ ናቸው

ቶማስ ታባኔ ከጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው እንደሚወርዱ አሳወቁ። የቀድሞ ሚስታቸውን በመግደል የተጠረጠሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለረዥም ወራት የቆየ ሕዝባዊ ተቃውሞ ካስተናገዱ በኋላ ነው ይህ ውሳኔያቸው የተሰማው።

ከመቼ ጀምሮ ከሥልጣናቸውን እንደሚያስረክቡ ባይናገሩም ፓርቲያቸው ግን ከማከሰኞ ጀምሮ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቃለ መሃላ ይፈጽማል ብሏል።

ከ80 ዓመቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር በመኖር ላይ የምትገኘው አዲሷ ሚስታቸው ከግድያው ጋር በተያያዘ ተከስሰው ፍርድ ቤት የቀረቡት በየካቲት ወር ነበር።

ሁለቱም ግን በግድያው እጃችን የለበትም ሲሉ አስተባብለዋል።

የቶማስ ታባኔ የቀድሞ ባለቤት ሊፖሌሎ ታባኔ በሽጉጥ የተገደሉት ከሦስት ዓመታት በፊት ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፖለቲካዊ ባልሆነና ከቤት ውስጥ ግድያ ጋር በተያያዘ ፍርድ ቤት መቅረባቸው በስልጣን ላይ ያሉ የመጀመሪያው አፍሪካዊ ያደርጋቸዋል።

ሁኔታው በደቡብ አፍሪካ ተከባ የምትገኘውን ትንሿን ሌሴቶ ያስደነገጠ ሆኗል።

ከዚህ ቀደም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከግድያው ጋር በተያያዘ በፖሊስ መጠየቃቸውን ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ የተቃዋሚ ደጋፊዎች በመዲናዋ ማሴሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን እንዲለቁ በሰልፍ ጠይቀው ነበር።

የተቃዋሚዎች ግፊት በመጨመሩም በወቅቱ ስልጣን እንደሚለቁ ቢያሳውቁም መቼ ሊሆን እንደሚችል አልተናገሩም ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለቤታቸውም ሆነ እሳቸው የተወነጀሉበትን ወንጀል ከማንሳት ተቆጥበው በጡረታ ራሴን አገልላሁ ነበር ያሉት።

ሊፖሌሎ ታባኔ

የፎቶው ባለመብት, Lesotho Times

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀድሞ ባለቤት ሊፖሌሎ ታቤን በሌሴቶ መዲና ማሴሮ በሚገኘው ቤታቸው ጥይት ተተኩሶባቸው የተገደሉት ከሦስት ዓመት በፊት ነበር።

በወቅቱም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለበዓለ ሲመታቸው ሁለት ቀናት ሲቀራቸው ነበር ግድያው የተፈጸመው ተብሏል፤ መረር ያለ የፍች ሂደትም ላይ ነበሩ።

በወቅቱም ከአሁኗ ባለቤታቸው ጋር አብረው ይኖሩ ነበር ተብሏል።

ነገር ግን ሊፖሌሎ በወቅቱ ቀዳማዊት እመቤት ማን ተብሎ ይጠራ የሚለውንም ጉዳይ ወደ ፍርድ ቤት ወስደውት፤ የቀዳማዊ እመቤት ለሳቸው ይገባል በሚል ተወስኗላቸው ነበር።

ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለበዓለ ሲመታቸው ሁለት ቀን ሲቀራቸው በመገደላቸው ምክንያት የአሁኗ ባለቤታቸው በክብረ በዓሉ ላይ ተገኝተዋል።

ከሁለት ወራት በኋላም ከአሁኗ ባለቤታቸው ጋር በሮማውያን ካቶሊክ ስነ ስርአት መስረት ጋብቻቸውን ፈፀሙ።

ማሳየህ ታባኔ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ቀዳማዊቷ እመቤት ማሳየህ ታባኔ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀድሞ ባለቤት ክስ ተመስርቶባቸው በ2ሺ ብር ዋስ ወጥተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ቀዳማዊቷ እመቤት የቤተሰቡ ቅርብ የሆነውን ታቶ ሲቦላን በመግደል ሙከራም ክስ ተመስርቶባቸዋል።

ታቶ ሲቦላ በወቅቱ የቀድሞዋ ቀዳማዊት እመቤት ሲገደሉ የአይን እማኝ ነበርም ተብሏል።