ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡ በአሜሪካ 100ሺህ ሰዎች በቫይረሱ ሳቢያ ሊሞቱ እንደሚችሉ ትራምፕ አስጠነቀቁ
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በአገራቸው በቫይረሱ ሳቢያ 100 ሺህ ሰዎች ሊሞቱ እንደሚችሉ አስጠነቀቁ።
ትራምፕ አስተዳደራቸው የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ዝንጉ ሆኖ ነበር የሚለውን ትችት እንደማይቀበሉም ተናግረዋል።
እስካሁን በአሜሪካ ከ67 ሺህ ሰዎች በላይ በወረርሽኙ ሳቢያ ህይወታቸውን ተነጥቀዋል።
ትራምፕ አክለውም የፈረንጆቹ ዓመት ከመጠናቀቁ በፊት ለኮቪድ-19 ክትባት ዝግጁ እንደሚደረግ ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ የዘርፉ ባለሙያዎች ክትባት ለማግኘት ከ12 እስከ 18 ወራት እንደሚያስፈልግ ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።
"በዚህ ዓመት መጨረሻ ላይ ክትባት እንደሚኖረን እርግጠኛ ነን" ሲሉ ትራምፕ ለፎክስ ኒውስ ተናግረዋል።
በትራምፕ ሃሳብ ከማይስማሙት መካከል ጉምቱ የጤና ባለሙያዎች አሜሪካዊው ዶክተር አንቶኒ ፋውቺ እና የእንግሊዝ የህክምና ኃላፊ ክሪስ ዊቲይ ይገኙበታል።
ዶክተር ፋውቺ ክትባት ለማግኘት ቢያንስ 18 ወራት ያስፈልጋሉ ያሉ ሲሆን፤ ክሪስ ዊቲይ በበኩላቸው በሽተኞችን ለማከም የሚረዳ መድኃኒትም ሆነ ክትባት በዚህ ዓመት የማገኘት እድል በጣም ጠባብ ነው ሲሉ ከአንድ ወር በፊት ተናግረው ነበር።
ትራምፕ አስተዳዳራቸው "ትክክለኛውን ነገር በመከውን" የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር ጥረት ማድረጉን ተናግረዋል። ይልቁንም ለቫይረሱ ስርጭት የቻይናን መንግሥት ተጠያቂ አድርገዋል።
"ትልቅ ስህተት የሰሩ ይመስለኛል [ቻይናውያን]፤ ስህተታቸውን አምነው መቀበል አልፈለጉም። ወደዚያ ማቅናት ፈልገን ነበር ግን አልፈቀዱልንም" ብለዋል ትራምፕ።
የአሜሪካ መንግሥት መረጃው እያለው ቫይረሱ በአገሪቱ ስለመከሰቱ ለሕዝቡ ይፋ አላደረገም ለሚለው ክስም ምላሽ ሰጥተዋል።
ትራምፕ ለዚህ ክስ የአገራቸው የደኅንነት ቢሮን ተጠያቂ አድርገዋል። ፕሬዝድንቱ እንደሚሉት ከሆነ እስከ ጃነዋሪ 23 (ጥር 24) ድረስ የደህንነት ቢሮ ለአስተዳዳራቸው አለማሳወቁን ተናግረዋል።
እንደ ሲኤንኤን እና ኤቢሲ ያሉ የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን የአሜሪካ የደኅንነት ቢሮ ኮሮናቫይረስ በአሜሪካ ስለመከሰቱ ጀነዋሪ 3 (ታህሳስ 24) ላይ መረጃው ነበረው።