ጀርመን ከሁለት ሰው በላይ እንዳይሰበሰብ እገዳ ጣለች

የፎቶው ባለመብት, EPA
ጀርመን የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ሲባል ከሁለት ሰው በላይ የሚደረግን ማንኛውንም መሰባሰብ በይፋ ከልክላለች።
ቻንስለሯ አንጌላ ሜርኬል ትናንት ባስተላለፉት መልዕክት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት "የራሳችን ባህሪ ከሁሉም ነገር የበለጠ ውጤታማ ነው" ብለዋል።
ጀርመን የውበት ሳሎኖችንና ሌሎች ብዙም አሰስፈላጊ ያልሆኑ የተባሉ ሱቆችን ቀደም ብላ ዘጋግታለች።
ከሁለት ሰው በላይ መሰባሰብን የሚከለክለው ጠንከር ያለው እገዳ ከተላለፈ ከጥቂት ቆይታ በኋላ የመራሄተ መንግሥቷ ጽህፈት ቤት ቻንስለሯ ራሳቸውን ለይተው እንዳሉ አስታውቋል።
ባለፈው አርብ ቻንስለር አንጌላ ሜርኬልን የሕክምና ምርመራ ያደረገላቸው ሃኪም በቫይረሱ መያዙ ተረጋግጧል። ቃል አቀባዩ እንዳስታወቁት የ65 ዓመቷ ቻንስለር በቀጣዮቹ ቀናት ተከታታይ ምርመራዎች እየተደረጉላቸው ከቤት ሆነው ሥራቸውን የሚሰሩ ይሆናል።
የአውሮፓ ግዙፍ ምጣኔ ሃብት ባለቤት የሆነችው ጀርመን እስካሁን 18 ሺህ 610 የሚሆኑት ዜጎቿ በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን 55 ዜጎቿ ደግሞ ለህልፈተ ሕይወት ተዳርገዋል።
ሰዎች አንድ መኖሪያ ቤት ውስጥ በጋራ የሚኖሩ ቤተሰብ ካልሆኑ ወይም ደግሞ የሥራ ጉዳይ አገናኝቷቸው ካልሆነ በስተቀር ሦስት ወይም ከዚያ በላይ ሆኖ መሰባሰብ ፈጽሞ የተከለከለ ነው።
ይህን መመሪያ ተላልፎ በተገኘ ግለሰብ ላይም ፖሊስ አሰፈላጊውን እርምጃና ቅጣት እንዲወስድ ትዕዛዝ ተሰጥቶታል።
ምግብ ቤቶች ክፍት የተደረጉ ሲሆን፤ ምግብ ይዞ መሄድ እንጅ እዚያው መመገብ አይፈቀድም። በሁሉም የጀርመን ግዛቶች ሁሉም ክልከላዎች የሚተገበሩ ሲሆን እገዳው ለሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ይቆያልም ተብለሏል።
"ዋናው ዓላማችን ቫይረሱን ለመከላከል ጊዜ ለማግኝት ነው" ያሉት ቻንስለር ሜርኬል "ሰዎች ከራሳችን ቤት ውጭ ያለን ንክኪ ሙሉ በሙሉ ማስቀረትና ከሰው ጋር ያላቸውን ማኅበራዊ እርቀትም በአንድ ነጥብ አምስት ሜትር መገደብ አለባቸው" በማለት አሳስበዋል።













