ሳዑዲ አረብያ ሦስት የንጉሣዊው ቤተሰብ አባላትን አሰረች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ሳዑዲ አረቢያ የልዑል አልጋወራሹን ሞሐመድ ቢን ሳልማን ታናሽ ወንድምን ጨምሮ ሦስት የአገሪቱ ልዑላንን ማሰሯን ኒዮርክ ታይምስና ዋል ስትሪት ጆርናል ዘገቡ።
ዘገባው እንደሚያመለክተው ልዑላኑ የታሰሩት ትናንት አርብ ጠዋት ነው።
ከታሰሩት ልዑላን መካከል ሁለቱ በሳዑዲ ዘውዳዊ ግዛት ውስጥ ከፍተኛ ተፅእኖ ያላቸው ሲሆኑ ለልዑላኑ መታሰር ምክንያቱ ምን እንደሆነ እስካሁን አልታወቀም።
ቢሆንም ግን ነገሩ ከልዑል አልጋወራሽ ሞሐመድ ቢን ሳልማን ጋር የተያያዘ እንደሆነ እየተገለፀ ነው።
እንደ አውሮፓውያኑ በ2017 በልዑል አልጋወራሽ ቢን ሳልማን ቀጭን ትዕዛት ትውልደ ኢትዮጵያዊውን ባለሃብት ሼክ ሞሐመድ አሊ አላሙዲንን ጨምሮ በርካታ የሳዑዲ ንጉሣዊያን ቤተሰብ አባላት የሆኑ ታላላቅ ሰዎች፣ ሚኒስትሮችና ባለሃብቶች በሪያዱ ሪትዝ ካርልተን ሆቴል መታሰራቸው የሚታወስ ነው።
ሞሐመድ ቢን ሳልማን በ2016 በአባታቸው በሳዑዲው ንጉሥ፤ ልዑል አልጋወራሽ ተብለው መሾማቸውን ተከትሎ የሳዑዲ ፈላጭ ቆራጭ ሆነዋል።
ሳዑዲ ያሰረቻቸው ልዑላን የልዑል አልጋወራሽ ቢን ሳልማን ታናሽ ወንድም የሆኑት ልዑል አህመድ ቢን አብዱልአዚዝ፣ የቀድሞ ልዑል አልጋወራሽ ሞሐመድ ቢን ናይፍ እና ልዑል ናዋፍ ቢን ናይፍ ናቸው።
ሞሐመድ ቢን ናይፍ በልዑል ቢን ሳልማን ትዕዛዝ 2017 ላይ በቤት ውስጥ የቁም እስረኛ እስከተደረጉበት ጊዜ ድረስ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ሲያገለግሉ ነበር።
የዋልስትሪት ዘገባ እንደሚያመለክተው ጥቁር ልብስ የለበሱና የፊት ጭምብል ያደረጉ ጠባቂዎች ወደ ልዑላኑ መኖሪያ ቤት በመሄድ ቤታቸውን በርብረዋል።
በ2016 እጅግ ወግ አጥባቂ በሆነችው ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ማሻሻያዎችን እንደሚያደርጉ ቃል የገቡት ሞሐመድ ቢን ሳልማን በጊዜው በከፍተኛ ሁኔታ ዓለም አቀፍ አድናቆት ተችሯቸው ነበር።
ነገር ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ ስማቸው ከሳዑዲው ጋዜጠኛ የጀማል ኻሾግጂ ግድያን ጨምሮ ከብዙ ቅሌቶች ጋር እየተነሳ ነው።












