ጋና፡ ውጤት ለማሻሻል ወሲብን ተተቅመዋል የተባሉት የዩኒቨርሲቲ መምህራን ታገዱ

ራንስፎርድ ግያምፖ እና ፐል ቡታኮር

ወሲባዊ ትንኮሳ ሲፈፅሙ በቢቢሲ ጋዜጠኞች በድብቅ የተቀረፁት ሁለት ጋናውያን መምህራን የለምንም ደሞዝ ከሥራቸው እንዲታገዱ እንደተወሰነባቸው ተገለጸ።

በጋና ዩኒቨርሲቲ መምህራን የሆኑት ፕሮፌሰር ራንስፎርድ እና ዶክተር ፖል ክዋሜ ቡታኮር 'ሴክስ ፎር ግሬድ' የተሰኘው የምርመራ ዘገባ ላይ እንደተማሪ ሆነው በቀረቡት ሪፖርተሮች ላይ ወሲባዊ ትንኮሳ ሲፈፅሙ ተቀርፀዋል።

ራንስፎርድ ግያምፖ ለስድስት ወራት ከስራ የታገዱ ሲሆን ፖል ቡታኮር ደግሞ ለአራት ወራት ከስራቸው ተገልለው እንዲቆዩ ዩኒቨርሲቲው ወስኗል።

አጣሪ ኮሚቴው ማስረጃዎቹን ከማጋለጡ በፊት ድርጊታቸውን እንዲያምኑ ለፕሮፌሰር ግያምቦ እና ዶክተር ቡታኮር የጋና ዩኒቨርሲቲ ጥሪ አቅርቦ ነበር።

ይሁን እንጂ ሁለቱም የዩኒቨርሲቲው መምህራን "ድርጊቱን አልፈፀምንም" ሲሉ ውንጀላውን በመቃወም ክደውታል።

በተመሳሳይ በዚሁ የቢቢሲ የምርመራ ዘገባ ላይ በድብቅ የተቀረፁት በናይጄሪያ የሚሰሩ መምህራንም ከሥራቸው መታገዳቸው ይታወቃል።

በናይጄሪያ ሌጎስ ዩኒቨርሲቲ ፣ ዶክተር ቦኒ ፌስ ኢግቤኔጉ እና ዶክተር ሳሙዔል ኦላዲፖ የተባሉት ሁለት መምህራንን ከሥራቸው ያገደ ሲሆን ይህንኑ የሚመረምር ኮሚቴ አቋቁሟል።

በምዕራብ አፍሪካ በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ የተሰራው የቢቢሲ የምርመራ ዘገባ መምህራኖች የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል ወሲብን እንደመደራደሪያነት እንደሚያቀርቡ ያሳያል።

ማሳሰቢያ : ይህ ታሪክ ግልጽ ወሲባዊ ቃላት አሉበት

በዘጋቢ ፊልሙ ውስጥ ዶክተር ፖል ቡታኮር ተማሪ መስላ የመጣችውን ሴት ሪፖርተር በድብቅ ጾታዊ ግንኙነት እንዲመሰርቱ ጥያቄ ሲያቀርብ ይታያል። ቀጥሎም ይህንን ካደረገች የትምህርት ሕይወቷ የተሳካ እንደሚሆን ይገልጻል።

ፕሮፌሰር ራንስፎርድ ግያምፖ ደግሞ ለሪፖርተሯ የአግቢኝ ጥያቄ ሲያቀርቡ ይታያል። አስከትለው ደግሞ ከየትኛው ትምህርት ቤት እንደመጣች ጠይቀዋት ስትመልስላቸው ከዛ ትምህርት ቤት የሚመጡ ሴት ተማሪዎች 'የወንድ ብልት' እንደሚያስደስታቸው መስማታቸውን ይገልጻሉ።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, በምዕራብ አፍሪካ አገራት ያሉ የዩንቨርስቲ መምህራን በተማሪዎቻቸው ላይ የሚፈጽሙት ወሲባዊ ትንኮሳ በቢቢሲ ምርመራ ተጋለጠ።

ዘጋቢ ፊልሙ ከተላለፈ በኋላ በጋና እና ናይጄሪያ ከፍተኛ ቁጣና ተቃውሞ ተቀስቅሶ የነበረ ሲሆን የጋና ዩኒቨርሲቲ መምህራኑ ምርመራው እስኪጠናቀቅ ያለምንም ክፍያ ከስራቸው ታግደው እንዲቆዩ ተደርገው ነበር።

ባሳለፍነው ጥቅምት ወር ለእይታ የበቃውን የቢቢሲ የምርመራ ዘገባ ተከትሎ የጋና ዩኒቨርሲቲ የዲሲፕሊን ኮሚቴ ምርመራውን ከጀመረ ወራት የተቆጠሩ ሲሆን ከትናንት በስቲያ (ሰኞ) ባስተላለፈው ውሳኔ ሁለቱም መምህራን የዩኒቨርሲቲውን ህግና ደንቦች ጥሰዋል ብሏል።

ቅጣታቸውን ከጨረሱ በኋላም ስለዩኒቨርሲቲው የጾታዊ ትንኮሳ ሕጎች ስልጠና እንዲወስዱ የሚደረግ ሲሆን ጸባያቸው ታይቶ ደግሞ ወደ ማስተማር ስራቸው ሊመለሱ እንደሚችሉ ኮሚቴው ገልጿል።

ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታትም ቁጥጥር ይደረግባቸዋል ብሏል ኮሚቴው።

በዩኒቨርሲቲ መምህራኑ ላይ የተላለፈው ውሳኔ በዋና ከተማዋ አክራ የተቀላቀለ ስሜትን እንደፈጠረ በቦታው የሚገኘው የቢቢሲ ሪፖርተር ቶማስ ናዲ ገልጿል።

አንዳንዶች ውሳኔው እጅግ የሚያሳዝንና እንደውም ሌሎችንም የሚያበረታታ እንደሆነ ገልጸዋል።

'' እስከዛሬ ሲደረግ የነበረውን ምርመራ ቀልድ የሚያስመስለው ውሳኔ ነው የተላለፈው። ስድስትና አራት ወራት ብቻ ያለደመወዝ ከስራ ማገድ ማለት እኮ ዓመታዊ እረፍት ወሰደው እንዲዝናኑ እንደማድረግ ነው። ይሄ ችግር አሁንም መፍትሄ አላገኘም'' ብላለች አንዲት ቢቢሲ ያነጋገራት የከተማዋ ነዋሪ።

አንዳንዶች ደግሞ ተገቢው ውሳኔ በመተላለፉ ደስተኞች እንደሆኑ ገልጸዋል።

'' ለእኔ ዩኒቨርሲቲው ያደረገው ነገር ለተማሪዎች ብርታት የሚሆንና ለአስተማሪዎች ደግሞ ማስጠንቀቂያ ነው'' ብሏል አንድ የዩቪርሲቲው ተማሪ።

የቢቢሲን የምርመራ ዘገባ ተከትሎ የናይጄሪያ ምክር ቤት በዩኒቨርሲቲዎች የሚፈጸሙ ጾታዊ ትንኮሳዎች ላይ ሕግ ለማውጣት ሰኞ ዕለት ውይይቱን የጀመረ ሲሆን በቀረበው ረቂቅ መሰረት ጥፋተኛ ሆነው የተገኙ ግለሰቦች እስከ አምስት አመት በሚደርስ እስራት እንዲቀጡ ሀሰብ ቀርቧል።